Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሽመልስ አብዲሳ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የ2015 ዓ.ም አዲስ ዓመትን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

እንኳን አደረሳችሁ ማለት የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባሕሪ መሆኑን ጠቅሰው÷ዘመን  መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ እርስ በርሳችን የምንለዋወጠው የመልካም ምኞት መገለጫ የሆኑ መልዕክቶች ግን ትልቅ ትርጉም አላቸው ብለዋል።

የጊዜ ዑደት ሆኖ ሰኮንዶች ወደ ደቂቃ፣ ደቂቃዎች ወደ ሰዓታት፣ ሰዓታትም ወደ ቀን፣ ቀናት ወራትን፣ ወራት ተደምረው ዓመት ይሆኑና አዲስ ዓመትን እንቀበላለን።

በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ የምናስተናግደው ሀዘንና ደስታ፣ ድልና ፈተና፣ ስኬትና ውድቀት በጊዜና ቦታ ዑደት ይበየናል። የሆነ ሆኖ ግን ዕድሎችም ይሁኑ ተግዳሮቶች፣ ሀዘንና ደስታን እንደየአመጣጠቸው በማስተናገድ፣ ከሕይወት ተሞክሮዎች ትምህርት በመቅሰምና በመቀመር ራሳችንን ለአዲስ ተስፋና ራዕይ ማዘጋጀት ሰውኛ ነው።

በአዲሱ ዓመት ከምንም በላይ ከመልካም ተሞክሮዎቻችንና ከፈተናዎቻችን ትልቅ ትምህርት በመውሰድ፣ ተሰፋን በመሰነቅ ለአዲስ ሕይወት ራሳችንን የምናዘጋጅበት ይሆናል። ተለዋዋጭ በሆነ የጊዜ ዑደት ውስጥ የሚያጋጥሙን ፈተናዎችና መልካም ዕድሎች ሁሉ በማለፍ አዲስ የሕይወት ተስፋን የሚያሰንቅ አዲስ ዓመት መድረስ መታደል ነው።

ስለሆነም ለመላው የኦሮሞ ሕዝብ፣ በአገር ውስጥና በውጪ ላላችሁ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን በሙሉ ዕድለኞች ናችሁና እንኳን ለ2015 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሠላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ።

2014 ዓ.ም እንደ ሀገር በርካታ ድሎችና ፈተናዎችን ያስተናገድንበት ዓመት ነበር።

ከውስጥና ከውጪ የተሸረቡብን ሴራዎችና የተዘረጉ የጥፋት ወጥመዶች ለዘመናት ያዳበርናቸውና እርስ በርሳችን ያሰናሰሉንን እሴቶቻችንን በመሸርሸር አገር ማፍረስን  ያለመ ነበር።

እነዚህ የውስጥና የውጪ ጠላቶቻችን እንዳሰቡት ባይሆንም ቅሉ በወጠኑት የግጭት ሴራ የዜጎቻችንን ውድ ሕይወት አጥተናል፣ በዚህም በበርካቶች ቤት ሃዘን ገብቷል።

በቀላል ዋጋ የማይገመት ንብረት ወድሟል። በተጨማሪም ተፈጥሮ የለገሰችን  ሀብቶቻችንን ተጠቅመን ከድህነት ለመላቀቅ የምናደርገውን ጥረት ለማጨናገፍ አደገኛ ሴራዎች ሲሸረብብንም ቆይቷል።

ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆኖ፣ የፖለቲካ ሴራቸው የከሸፈባቸው አካላት ኢኮኖሚያዊ አሻጥር በመፈፀም ሕዝባችንን በኑሮ ውድነት ለማሰቃየት ያለተደረገ ጥረት የለም።

የዚህ የኢኮኖሚ አሻጥር ዋና ዓላማ ሕብረተሰቡ በኑሮ ውድነት ተማሮና ተነሳስቶ አገሩን በራሱ ላይ እንዲያፈርሰ ታሳቢ ያደረገ ሴራ ቢሆንም፣ ሕዝባችን አርቆ አሳቢ  በመሆኑ  የጠላት እቅድ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል።

ከሰው ሰራሽ ፈተናዎች በተጨማሪ፣ በ2014 ዓ.ም ዝናብ አጠር በሆኑ  በአርብቶ አደር አከባቢ የተፈጠረው ድርቅ ቀላል የማይባል  ፈተና የደቀነብን ነበር። በርካታ ፈተናዎች ያጋጠሙ ቢሆንም ከጠላቶቻችን የተወረወሩብን የክፋት ጦር በዘመናት ባካበትነው አንድነታችን መቀልበስ ችለናል፡፡ በመሆኑም ለዬትኛውም ተጽዕኖ የማንበረከክ ሕዝቦች ስለመሆናችን ለዓለም ማህበረሰብ አስመስክረናል።

በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ፈተናዎችን ወደ መልካም ዕድል የመቀየር አቅምም አዳብረናል። በፈተና ውስጥ ሆኖ የፈተና መንስኤዎችን በማስወገድ ለዘላቂ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መደላድል መሰረት መጣል እንደሚቻል ትልቅ ትምህርትም ተወስዶበታል።

የቱንም ያህል ፈተናዎች ቢበዙም ካለምነው የብልፅግና ጉዞ ሊገቱን እንደማይችሉ ማረጋገጥ የቻልንበት ዓመት ነበር። ኢትዮጵያ በጫና ብዛት የምትንበረከክ፣ በታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራ የምትፈርስ አገር ሳትሆን በተግዳሮቶች እንደ አላት የምትጠነክር፣ በፈተና የምትፀና  መሆኗን በተግባር አይተናል።

ስለዚህ 2014 ዓ.ም ፈተና ብቻ ሳይሆን ለሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጉዞ ጠንካራ መሰረት የጣልንበት ዓመት ነበር። ተርበው እጅ ይሰጣሉ በሚል የኢኮኖሚ ማዕቀብ ሲያሴሩብን፣ በበጋ ስንዴ አምርተን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ከእኛም ተርፎ ወደ ውጪ ለመላክ እንደምንችል አረጋግጠናል።

በአንድ በኩል ህልውናችንን ለማስጠበቅ የተቃጣብንን ጦርነት በመመከት በሌላ በኩል ደግሞ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከ20 ሺህ በላይ የመሰረተ ልማት ፕሮጅክቶችን ሰርተን በማጠናቀቅ ለብልፅግና ጉዞዓችን ምቹ ሁኔታን ፈጥረናል።

በአጠቃላይ በ2014 ዓ.ም ብዙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች የገጠሙን ቢሆንም ከብልፅግና ጉዞዓችን ዝንፍ ሳንል ከግባችን ለመድረስ ያሳየነው ቁርጠኝነትና ትጋት የ2015 ዓ.ም እቅዳችን ለማሳካት ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት ይሆናል። አዲሱ ዓመት ብዙ ተስፋዎችንና ዕድሎችን ይዞ ይመጣል።

በ2014 ካጋጠሙን ተግዳሮቶች ብዙ ተምረናል። ባሳለፍነው ዓመት በተቀመረ ተሞክሮና በተቀሰመ ትምህርት ተስፋችንን እውን የምናደርግበት፣ መልካም ዕድሎችን የምናሰፋበት መሆን ይገባል። ከሁሉ በላይ የጠላቶቻችን የጥፋት ሴራ ትኩረት ከሆኑ ነጥቦች መካከል ብዘሃነታችን ዋንኛው መሆኑን ካሳለፍነው ዓመት ልምድ ትልቅ ትምህርት ለመውስድ ችለናል።

የጠላቶቻችንን የጥፋት ሴራ የምንመክትበት ጋሻችን ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት ነው። ብዘሃነታችን ጌጣችን ነው፤ በመሆኑም አንዳችን ለሌላችን አሌኝታ እንጂ ስጋት ሆነን አናውቅም። የእያንዳንዳችን ዕድልና ተስፋ የተሳሰረና የተሰናሰለ በመሆኑ የአንዳችን ጥቃት የሁላችንም ጥቃት ነው።

ጠላት ሲነዛ የነበረው የጥላቻ ትርክት በህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት በመተካት በመደመር እሳቤ አዲሱን ዓመት በተስፋ እንቀበል። እሴት አድርገንም እንኑርበት። በአዲሱ ዓመት ጠላቶቻችን ክፍተት እንዳያገኙ የሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት እሴቶችን በማጠናከር ዘላቂ ሀገራዊ ጥቅሞቻችን በጋራ የምናስጠብቅበት ሁለንትናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ ትኩረታችን ሊሆን ይገባል።

ሌላው የተጋላጭነታችን ምንጭ ድህነት መሆኑን ከ2014 ዓ.ም ብዙ ትምህርት ቀስመንበታል። ድህነት አንገት አስደፊ እድፍ ነው፡፡ ሠርተን ልንለውጥ ይገባል፡፡  ከድህነት ለመውጣት ሰፊ ዕድል አለን። ያሉንን የመልማት እምቅ ሃይላችን አሟጠን ከተጠቀምንባቸው ከጠላቶቻችንን የሚሰነዘሩብን ጥቃቶችን ለመመከት ሆነ ጫናዎቻቸውን ለመቋቋም የምንችልበት ክንድ ማጠናከር እንደምንችል ትልቅ ትምህርት እንወስዳለን።

ስለዚህ 2015 የመልማት ዕድሎቻችንን የምናሰፋበት፣ ምርታማነታችንን የምናሳድግበት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራና አጠቃቀማችን የምናጎለብትበት፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፈን ወደ ውጪ መላክ የምንጀምርበት ወሳኝ ምዕራፍ ስለሆነ ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል።

ከድህነት ተላቀን ሁለንትናዊ ብልፅግናን እውን ለማድረግ የስራ ባህላችንን ማጎልበት ይጠበቅብናል፡፡ የዳበረ ኢኮኖሚን የገነቡ፣ የህዝባቸውን ብልፅግናን ያረጋገጡ አገሮች የስራ ባሕላቸውን ያጎለበቱ ናቸው፡፡ በዚህ አዲስ አመት በስራ ባሕላችን ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ለራሳችን ቃል የምንገባበት ይሆናል። ሁለንተናዊ ብልፅግናን እውን ለማድረግ የስራ ሠዓት በማክበር፣ የአገልጋይነት ስሜት በማዳበር፣ ስርቆትን በመጠየፍ፣ የፈጠራ ስራን በማስፋት፣ ሕግና ስርዓትን ማክበርን እንደ መርሆ ልንጠቀምበት ይገባል።

በአጠቃላይ በአዲሱ ዓመት ሠርተን ውጤት የምናስመዘግብበት፣ ነግደን የምናተርፍበት፣ ሁለንትናዊ ብልፅግናን እውን ለማድረግ ጠንካራ መሠረት የምንጥልበት፣ ከሁሉም በላይ ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት በተጠናከረ ሁኔታ ሰርፆ ዘላቂ ሠላም የሚሰፍንበት ዓመት እንዲሆንልን እየተመኘሁ በድጋሚ እንኳን ለ2015 አዲሱ ዓመት በሠላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ።

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.