Fana: At a Speed of Life!

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በኮልፌ ቀራኒዮ ያስገነቡትን የመኖሪያ ቤትና ሱቆች አስረከቡ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ዘነበወርቅ፣ ዘውዴ ሜዳ አካባቢ ያስገነቡትን የመኖሪያ ቤቶችና ሱቆችን ለነዋሪዎች አስረከቡ።

ከሁለት ወር በፊት በአካባቢው ጉብኝት ያደረጉት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የነዋሪዎችን አስቸጋሪ ሁኔታ ተመልክተው የመኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

በ75 ቀናት ውስጥ 20 የመኖሪያ ቤቶች እና 15 ሱቆች ግንባታቸው ተጠናቆ ዛሬ ለነዋሪዎች ተበርክቷል።

የቤት ስጦታ የተበረከተላቸው በዋናነት የስጋ ደዌ ተጠቂዎች፣ አቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኞች ናቸው ተብሏል።

ግንባታው በ800 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ሲሆን÷ 20 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል ነው የተባለው።

ለነዋሪዎች የተበረከተው የአዲስ አመት የቤት ስጦታ ሶፋ ፣ አልጋ፣ ፍራሽ፣ የማብሰያ እቃዎችን ጨምሮ የመጸዳጃ እና የመታጠቢያ ክፍሎችን ያሟላ ነው።

በቤቶቹ ርክክብ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለነዋሪዎቹ  በአዲሱ መንደር ማዕድ አጋርተዋል፡፡

በርክክቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ቀዳማዊት እመቤቷ ዛሬ ለነዋሪዎች ያስረከቡት ብርሃን የመኖሪያ መንደር-1 የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን÷ በአካባቢው ብዙ የማህበረሰብ ክፍል መሰል ድጋፍ የሚፈልግ በመሆኑ ግንባታው በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

ግብረሰናይ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ድጋፍ እንዲያደርጉ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጥሪ አቅርበዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.