Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ ዓመት ተስፋና ምኞትን የምንሰንቅበት ብቻ ሳይሆን ለላቀ ድል የምንዘጋጅበት ነው- ር/መስተዳድር ይልቃል ከፋለ

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲሱ ዓመት ተስፋና ምኞትን የምንሰንቅበት ብቻ ሳይሆን ለላቀ ድል የምንዘጋጅበትና ወደ አንድ ሀገራዊ ስሜት የምንመጣበት ሊሆን ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ለኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለ2015 አዲሱ አመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም አዲሱ ዓመት የልማት እቅዶችን የምናሳካበት፣ ልዩነቶች በመቻቻል፣ በመደማመጥና በመነጋገር የሚፈቱበት፣ የኢትዮጵያ ሰላም በአንድነትና በህብረት የምናጸናበት እንዲሆን ሁሉም ዜጋ በትብብርና በአንድነት መቆም ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡

በአንድነት ስንቆም የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ድል አድርገን፣ ህልውናችን አጽንተን፣ ሀገራችን አስከብረን፣ የምንመኘው ሀገራዊ እድገት አረጋግጠን ትልቅ መሆን እንደምንችል አሳይተናል፣ አስመስክረናል ብለዋል።

የህዝቡን ህልውና ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ትግል በማድረግ ላይ እንገኛለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ዓመቱ ካለፈ ስህተቱ የማይማረውና ከሰላም ይልቅ ጦርነትን ብቸኛ ምርጫው ካደረገ ግፈኛና ወራሪ ቡድን ጋር በጽናት እየታገልን የምንቀበለው ዓመት ነውም ብለዋል በመልዕክታቸው።

“ነጻነትና ክብር ያለ ብርቱ ትግል፣ አሸናፊነትን ያለ መስዕዋትነት መጎናጸፍ አይታሰብም፣ በጋራ ትግላችን የጠላትን አከርካሪ ሰብረን የህዝብን ነጻነትና የሀገርን አንድነት በዘላቂነት እናፀናለንም“ ነው ያሉት።

በእብሪት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ ዳግም ወረራ የፈጸመውን ወራሪ ቡድን ፍላጎትና ምኞቱን አክሽፈን በድል አድራጊነት ለመዝለቅ መላ ኢትዮጵያውያን ለጥምር ጦሩ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሠላም፣ የጤና፣ የልማት፣ የአንድነትና የድል ዘመን እንዲሆን በራሳቸውና በክልሉ መንግሥት ስም መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.