Fana: At a Speed of Life!

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለመላው ኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ መጪው አዲስ ዘመንለኢትዮጵያውያን ሰላም፣ መቻቻል፣ መከባበርና መፈቃቀድ የሰፈነበት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያብሔራዊ ደኅንነት እና ጥቅም እንዲረጋገጥም ሁሉም ተባብሮ እና ተደማምጦ የሚሰራበት እንዲሆንም አሳስበዋል።

‹‹መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ፤ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤናና የስኬት እንዲሆን በራሴ እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች ስም መግለጽ እወዳለሁ›› ብለዋል፡፡

በተለይ የኢትዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በግዳጅ ላይ የምትገኙ የጀግናው የመከላከያ ሠራዊት እና የጥምር ጦሩ አባላት መላው ሕዝብ የሰላም አየር እንዲተነፍስ የሕይወት ዋጋ ጭምር እየከፈላችሁ በመሆኑ ክብር ይገባችኋል ብለዋል፡፡

ውድ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አዲሱ ዓመት ለሰላም በምትከፍሉት መስዋዕትነት በአዳዲስ የድል
ብሥራቶች የሚታጀብ እንደሚሆን በልበ ሙሉነት እገልጻለሁም ነው ያሉት፡፡

የተቋሙ አባላትም የሥጋት ቀጣና በሆኑ አውደውጊያዎች ጭምር በመሠማራት መረጃ በመሰብሰብ፣በመተንተንና ለሚፈለገው አላማ እንዲውል በማድረግ ሀገራዊ ግዳጃቸውን እየተወጡ በመሆኑ አክብሮቴና የአዲሱ ዘመን መልካም ምኞቴ በያሉበት ይድረሳቸው ብለዋል፡፡

በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ ሰላምን አበክራ ትሻለች፤የሰላሙ መንገድ ዛሬም ክፍት ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ይህን ባለመቀበል ጦርነትን የቀሰቀሱ አካላት ዛሬም የሰላምን ዋጋ ተረድተው በአዲስ ዓመት በአዲስ መንገድ እንዲጓዙ ኢትዮጵያ ጥሪ ታቀርባለች ያሉት አቶ ተመስገን፤ በሀገር ህልውና የተቃጣውን ጥቃት ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና የጥምር ጦሩ በብቃት መመከታቸውን ወደፊትም ይህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትም በተጠናቀቀው ዓመት ባከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች ዘመኑን የሚዋጁ ቴክኖሎጂዎች በመታጠቁና የላቀ ብቃት ያለው የሰው ኃይል አቅም በመገንባቱኢትዮጵያ ፈተናዎችን በአሸናፊነትና በጽናት እንድትሻገር ብርቱ ጉልበት ሆኗል፤ በእርግጥም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.