Fana: At a Speed of Life!

የዛፖሪዢያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ደኅንነት እንዳሳሰባቸው ፑቲን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን እና ከፈረንሳዩ አቻቸው ኢማኑዔል ማክሮን ጋር በዛፖሪዢያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ የደኅንነት ጉዳይ ላይ መክረዋል፡፡

ሩሲያ በዛፖሪዢያ የተከማቸው ጨረር አመንጪ የኒውክሌር ውጋጅ በሰው ሕይወት ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋጋት እንዳላት በዚህ ወቅት ተገልጿል።

ይህ ደግሞ ከዩክሬን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ሩሲያን ሥጋት ውስጥ እንደከተታት ነው የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን ከፈረንሳዩ አቻቸው ኢማኑዔል ማክሮን ጋር በሥልክ በነበራቸው ቆይታ ያነሱት።

ፑቲን አክለውም ዩክሬን ከምዕራባውያን በሚደረግላት የጦር መሣሪያ ድጋፍ በዶንባስ በሚገኙ ከተሞች ላይ የመሠረተ-ልማት ውድመት እየፈጸመች ነው ብለዋል፡፡

ጉዳዩ የአካባቢውን ነዋሪዎች ለእንግልት እና ስቃይ መዳረጉንም ነው በሥልክ በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት፡፡

ሩሲያ የኒውክሌር ማመንጫ ጣቢያውን ደኅንነት በተቻላት ሁሉ እየጠበቀች እንደሆነና ዩክሬን ከምታደርሰው ጥቃት እና ውድመት ግን በአስቸኳይ እንድትታቀብ ግፊት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ለማክሮን ገልጸውላቸዋል፡፡

መሪዎቹ በዛፖሪዢያ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ያንዣበበው የአደጋ ሥጋት የፖለቲካ ጉዳይ እንዳልሆነ የጋራ አቋም የያዙ ሲሆን፥ በዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ተሳትፎ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ሺንዋ ዘግቧል፡፡

ከቅርብ ሣምንታት ወዲህ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫው በሚገኝበት አካባቢ ጥቃቶች ሲፈጸሙ መቆየታቸው እና ይህም ከደኅንነት አንጻር ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ሥጋት ላይ እንደጣለው መገለጹ ይታወሳል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.