Fana: At a Speed of Life!

በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ 767 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን መታደጉን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሀገሪቱ የባህር ዳርቻ ጥበቃ ሀይልና ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር 767 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ህይወት መታደጉን አስታወቀ።

አደገኛ ከሆነው የሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ሰዋራ መረብ አደጋዎች ተርፈው የከፋ አደጋ ወደሚደርስበት የጂቡቲ የባህር ላይ ጉዞ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ስድተኞችን ህይወት ለመታደግ ኤምባሲው ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ 767 ስደተኞችን ማትረፍ ችሏል ነው የተባለው።

የጂቡቲ የባህር ዳርቻ ጥበቃ ሀይል እና ብሔራዊ ባህር ሃይል ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓ.ም በጂቡቲ የኦቦክ ክልላዊ መስተዳደር ራስ-ብር ከተባለው አካባቢ በመነሳት 196 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን አሳፍራ ወደ የመን የምትጓዝ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ጀልባን መያዙ ተገልጿል፡፡

ከ196ኙ መካከል 29ኙ ሴቶች ሲሆኑ በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለስደተኞቹ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም ሶስት የውጭ ዜጎችና አንድ ኢትዮጵያዊ በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት ተጠርጥረው ለፍርድ መቅረባቸው ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሕገ-ወጥ ጀልባዎችን በመጠቀም ከየመን ወደ ጂቡቲ እንዲሁም ከጂቡቲ ወደ የመን በሚያደርጉት ጉዞ በጅቡቲ የባህር ጠረፍ ክልል ተደጋጋሚ የጀልባ መገልበጥ አደጋዎች እየደረሱ በርካታ ዜጎች ለህልፈት እየተዳረጉ ነው ተብሏል፡፡

ኤምባሲው ዜጎች በሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተታለው ይህን አደገኛ የጉዞ መስመር እንዳይከተሉ አሳስቧል፡፡

የጂቡቲ የባህር ዳርቻ ጥበቃ ሀይል እና ብሔራዊ ባህር ሃይል ዜጎችን ለመታደግ ለሚያደርጉት ዘመቻ  ምስጋና መቅረቡንበጂቡቲ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.