Fana: At a Speed of Life!

በሙስና የተመዘበረ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ አሳግጃለሁ – ፍትሕ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፈው ዓመት በሙስና የተመዘበረ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ማሳገዱን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሙስና የተመዘበረ ገንዘብ፣ መሬት፣ ቤትና ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ሀብቶችን ተከታትሎ ማስመለሱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

በዚህም 10 ሺህ ካሬ ሜትር መሬትን ጨምሮ ከ88 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሁም ተሽከርካሪዎች እና መኖሪያ ቤቶች ተመልሰዋል ነው የተባለው፡፡

በክርክር ላይ ያሉና ክስ የተመሰረተባቸው የመንግስትና የሕዝብ ሃብቶች እንዲታገዱ መደረጉም ተመላክቷል፡፡

በዚሁ መሰረት÷ 701 ሚሊየን ብር ጥሬ ገንዘብ፣ ከ744 ሚሊየን ብር በላይ የሼር ገንዘብና የ27 ሚሊየን ብር ቦንድ እንዳይንቀሳቀስ በፍርድ ቤት መታገዱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከ41 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ታግዶ በፍርድ ቤት የክርክር ሂደት ላይ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የሙስና ወንጀሎች ውስብስብና ጊዜ የሚወስዱ ክርክሮችን የሚፈልጉ ስለሆኑ ክርክሩ እስከሚጠናቀቅ የተመዘበረ ሃብት እንዳይንቀሳቀስ መደረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በሙስና ተመዝብረዋል ተብለው የተያዙ 364 ተሽከርካሪዎች፣ 155 ቤቶች እና 617 የተለያዩ ማሽነሪዎችም በተመሳሳይ ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው እንዳይሰጡና እንዳይሸጡ ተደርጓል፡፡

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.