Fana: At a Speed of Life!

ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እናደርጋለን-አምባሳደር ፈኻድ አልሁማይዳኒ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ያለመኖሪያ በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ በኢትዮጵያ የሳዑዲ አምባሳደር ፈኻድ አልሁማይዳኒ ተናገሩ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ከሳዑዲ አምባሳደር ፈኻድ አልሁማይዳኒ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው ሚኒስትሯ ሁለቱ ሀገራት ለዘመናት የነበራቸው የመንግስታት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ወቅት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቅመ ደካሞች፣ ሴቶች፣ ህጻናት እና አካል ጉዳተኞችን በመደገፍ ረገድ እየተወጣ ያለውን ማህበራዊ ሃላፊነት በተመለከተ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

በተጨማሪም ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እየተደረገ ስላለው ሰብአዊ ድጋፍ እና ከሳዑዲ ተመላሽ ዜጎች እያጋጠማቸው ያለውን ፈተና በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህ ወቅትም ከሳዑዲ አረቢያ ለሚመለሱ እና በተለይም ለህጻናትና ሴቶች ሀገራቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር በሚችሉበት አግባብ ተጨማሪ ውይይት ማድረግ ስለሚቻልበት ሁኔታም መክረዋል።

አምባሳደር ፈኻድ አልሁማይዳኒ በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት አጋርነት እና ግንኙነት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህን የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር ለሁለቱ ሀገራት የጋራ እድገት በትብብር መስራት አስፈላጊ ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

አያይዘውም ያለ ስራ ፈቃድ በሳዑዲ አረቢያ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እነ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ከሚመለከተው አካል ጋር ምክክር በማድረግ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.