Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” መርሕ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” መርሕ በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት ለሚደረገው የሰላም ድርድር ሂደት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ጠየቁ፡፡

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በቤጂንግ ለሚገኙ የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት፣ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የካናዳ እና ኖርዌይ ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ግጭትና ችግሩ እንዲቋጭ በመንግሥት በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱን ለማስቀረትና ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያደረጋቸውን ጥረቶች አሸባሪው ህወሓት ረግጦ÷ ለሦስተኛ ዙር በትግራይ፣ በአማራ እና የአፋር ሕዝቦች ላይ አስከፊ ሰቆቃ እየፈፀመ መሆኑን አምባሳደሩ አስረድተዋል።

ለሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል በተጓጓዙ የምግብና የነዳጅ አቅርቦቶች ላይ ጭምር ዘረፋ እንደፈጸመ መናገራቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል።

በዓለም አቀፍ ሕግ የጦር ወንጀል የሆነውን ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ ሕጻናትን በጦርነቱ በመማገድ ግፍ እየፈፀመ መሆኑን በመጥቀስም፥ በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ዘንድ ተገቢው ጫና ባለመደረጉ የተነሳ የሽብር ቡድኑ የያዘውን አውዳሚ ባህሪ ቀጥሎበታልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፅኑ ፍላጎት እዳለው ጠቁመዋል።

“ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” በሚለው መርህ በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት ለሚደረገው የሰላም ድርድር ሂደት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.