Fana: At a Speed of Life!

የጨጓራ ህመም መንስዔ፣ ምልክቶች እና መፍትሄው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጨጓራ በአንጀታችን የመጀመሪያው ክፍል የሚገኝ የሰውነታችን አካል ሲሆን ዋና ስራውም ምግብን መፍጨት /ማላም/ ነው፡፡

የጨጓራ ህመም የሚባለው በጨጓራ ክፍል ላይ የሚመጣ የጨጓራ ግድግዳ መቆጣት /መጎዳት/ አንዳንድ ጊዜም መቁሰል ሲከሰት ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ኤፍሬም ሃይሌ÷ ስለ ጨጓራ ህመም ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

ህመሙ በተለያየ የማህበረሰብ ክፍል፣ በየትኛውም የዕድሜ ክልልና በማንኛው ፆታ ሊመጣ የሚችል ህመም ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

መንስኤው በርካታ መሆኑን ጠቅሰው፥ በተለይ ጨጓራ ባዶ በሆነበት ሰዓት ጨው፣ ቅመማቅመም እና በርበሬ የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ፣ የጨጓራ ግድግዳን እንደሚጎዳ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለተለያዩ ህመሞች የሚሰጡ መድሃኒቶች (መጠናቸው ሲበዛ)፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል አብዝቶ መጠቀም ፣ የጨጓራ ባክቴሪያ እና ሌሎች መንስኤ ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ዶክተር ኤፍሬም ሃይሌ ገለፃ ከጨጓራ ህመም ምልክቶች ውስጥ ምግብ ያለመፈጨት ስሜት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ ከበድ ያለ ሙቀት (በተለይ ጀርባ አካባቢ) እና የምግብ አለመስማማት ይጠቀሳሉ፡፡

ህመሙን ለመከላከልም መንስኤው ላይ ማተኮር እንደሚገባም ነው የሚናገሩት።

በዋናነትም አዘውትሮና አብዝቶ አልኮል አለመውሰድ ፣ ከሃኪም ትዕዛዝ ውጪ ለረጂም ጊዜ የሚወሰዱ መድሃኒቶችን ማስወገድ፣ የጨጓራ አሲድን ለመቀነስ ለተወሰነ ጊዜ የሚሰጡ መድሃኒቶችን ከሃኪም እውቅና ውጪ ህመም ሲሰማ በተደጋጋሚ መውሰድን ማስወገድ ለመከላከል እንደሚረዳ መክረዋል፡፡

አይነት እና ደረጃው ብዙ በመሆኑ ሕክምናውም ያን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ህመም ሲሰማ ወደ ህክምና በመሄድ ሃኪም ማማከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.