በበጀት ዓመቱ 280 የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት 280 የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
ከሁሉም ክልሎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሪጂኖችና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የተውጣጡ ከ900 በላይ አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች በታደሙበት መድረክ የ2015 ዓ.ም ዕቅድ ማስፈፀሚያ ስልቶችና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ምክክር እየተደረገ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሽፈራው ተሊላ÷ በተያዘው በጀት ዓመት 280 የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 204 የገጠር ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ 367 ሺህ 466 አዳዲስ ደንበኞችን ማፍራቱንም ነው የተናገሩት።
አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ በአማራና አፋር ክልሎች በደረሰው ጉዳት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ኪሳራ መድረሱን ዋና ስራ አስፈፃሚው አስታውሰዋል፡፡
አገልግሎቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት ጠግኖ ወደ አገልግሎት መመለስ እንደተቻለ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በ2015 ዓ.ም 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ደንበኞችን ለማፍራት እና ከኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ እንዲሁም ከልዩ ልዩ አገልግሎቶች 43 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን አንስተዋል፡፡’