አሜሪካ ለግብፅ የምትሰጠውን የ130 ሚሊየን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ከለከለች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ለግብፅ ልትሰጥ የነበረውን የ130 ሚሊየን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ለማቋረጥ መወሰኗን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ገለጹ።
አሜሪካ የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ የከለከለችው በግብፅ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ በመምጣቱ ነው ተብሏል፡፡
የመብት ተሟጋቾች ÷ ግብፅ በአሜሪካ ምክር ቤት መስፈርት መሰረት ዕርዳታ ለማግኘት ማሟላት ያለባትን ቅድመ ሁኔታ አላሟላችም የሚል ሀሳብ በማቅረብ፥ ተጨማሪ የ300 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንድታጣ ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ አሁንም በግብፅ የፖለቲካ እስረኞች ስቃይ እንደሚደርስባቸው እና አንዳንዶችም ደብዛቸው እንደሚጠፋ ገልጸዋል፡፡
የመካከለኛው ምሥራቅ ዴሞክራሲ ላይ የሚሰራ አንድ ተሟጋች ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ሴት ቢንደር የተባሉ ግለሰብም ÷ ግብፅ በሰብዓዊ መብት እና በፖለቲካ እስረኞች አያያዝ ላይ ከፍተኛ ችግር ያለባት አገር መሆኗን መስክረዋል፡፡
አሜሪካ በየዓመቱ ለግብፅ የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር የበጀት ድጋፍ እንደምትመድብ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ግብፅ ከአሜሪካ ከፈረንጆቹ 1946 ጀምሮ እስከ 2020 ድረስ ከ85 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ድጋፍ ማግኘቷንም በግብጽ የአሜረካ ንግድ ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።
የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ ÷ በግብፅ ምንም ዓይነት የፖለቲካ እስረኞች የሉም ሲሉ እንደሚናገሩም ዘገባው ጠቁሟል።
የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ ÷ በግብፅ ምንም ዓይነት የፖለቲካ እስረኞች የሉም ሲሉ እንደሚናገሩም ዘገባው ጠቁሟል።