Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ አስተዳደር የአዲሱን ሥርዓተ ትምህርት መጻሕፍት ላዘጋጁ አካላት ዕውቅና እና ሽልማት ሰጠ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲሱን ስርዓተ-ትምሕርት ማስጀመሪያ እና የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሐፍት ላዘጋጁ አካላት የዕውቅና እና ሽልማት አሰጣጥ መርሐ-ግብር አከናወነ።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የአዲሱን ስርዓተ ትምሕርት መጀመርና የተማሪዎች መማሪያ እና የመምህር መምሪያ መፅሐፍት ዝግጅት ላይ ለተሳተፉ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ባለድርሻ አካላት የዕውቅና እና የሽልማት አሰጣጥ ስነስርአት ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ “ክረምቱን ከሞቀ ቤታችሁ ብርድና ቁር ሳይበግራችሁ የተሰጣችሁን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት የየድርሻችሁን አሻራ ለሀገር ሁለንተናዊ ግንባታና የትውልድ ስብዕና ቀረጻ ላይ ያበረከታችሁ ባለሙያዎች ከተማ አስተዳደሩ ለልፋታችሁ እውቅና በመስጠት ያመሰግናችኋል” ብለዋል።

ስርአተ ትምሕርቱ ትውልድን በሚፈለገው ደረጃ ለማነፅና ሀገርን በአብሮነት ቆሞ ለመገንባት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም እንደታየው ሁሉም በየራሱ መነፅር የሚመለከት ትውልድ የፈራበት ሳይሆን አብሮ መኖርን የሚያጠናክር የሀገር በቀል እውቀትን የሚረዳ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶት የተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተጨማሪም ስርአተ ትምሕርቱ ወደ መማር ማስተማር የተቀየረበት መንገድ አስተማሪ መሆኑን ጠቅሰው፥ ሁሉም በተሰማራበት ሁሉ የበኩሉን ተደማሪ አሻራ ማኖር ይጠበቅበታል ማለታቸውን የከንቲባ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

ሀገር የሚገነባው ሁሉም በየደረጃው የበኩሉን ሳይሰስት ፊት ለፊት ምሳሌ ሆኖ መስራት ሲችል በመሆኑ፥ ይህን ስራ ለአማካሪዎች ከመስጠት ይልቅ በባለቤቶቹ መሰራቱ በጥራትም ሆነ በገንዘብ ውጤታ መሆን እንዳስቻለም ጠቁመዋል።

በቀጣይ የትውልድ ስብዕና ግንባታ ላይ በሚሰሩ ስራዎችም ከተማ አስተዳደሩ አብሯችሁ ይቆማል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ከተማ ትምሕርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው አዲሱ ስርአተ ትምሕርት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተከለሰው የትምሕርት ፖሊሲና ስርዓተ -ትምሕርት ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

አዲሱ ስርዓተ -ትምሕርት በአጠቃላይ የመጽሐፍት ህትመት ስራው ከ1 ቢሊየን ብር ባነሰ ወጪ የተዘጋጀ ሲሆን፥ በ17 ሺህ 300 የግልና የመንግሥት ትምሕርት ቤቶች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.