Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ወጣቶችን የማስተሳሰር መርሐግብር ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ የኢትዮጵያውያንና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ወጣቶችን የማስተሳሰር መርሐ ግብር ይፋ አድርጓል ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አባል እና የብሔራዊ ኮሚቴው ጸሐፊ አክሊሉ ታደሰ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ሀገራት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ፍስሐ ሻወል በጉዳዩ ላይ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

አክሊሉ ታደሰ በመግለጫቸው÷ የአፍሪካ ሀገራት ወጣቶችን የማስተሳሰር መርሐ ግብር ይፋ መሆኑን ተከትሎ ከዛሬ ጀምሮ ሦስት ኩነቶች ይከወናሉ።

በዚሁ መሠረት÷ ዛሬ በ13 የአፍሪካ ሀገራት ኤምባሲዎች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጋር ባላቸው ታሪካዊ ግንኙነት በኩባ እና ደቡብ ኮሪያ ኤምበሲዎች የማዕድ መጋራት “አፋሪካ ፋራተርኒቲ ዲነር ፕሮግራም” ይካሄዳል ብለዋል፡፡

በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ ኢትዮጵያን እና ሀገራቱን የሚያስተሳስሩ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል፡፡

ሁለተኛው መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም የሚጀምረው “ፕላንት አፍሪካን ፋራተርኒቲ” የተሰኘው ኩነት ሲሆን÷ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በጎረቤት የአፍሪካ ሀገራት የችግኝ ተከላ፣ ውይይት እና ጉብኝት የሚያደርጉበት ነው ተብሏል፡፡

ለዚህም ኩነቱ በሱዳን ፣ ደቡብ ሱዳን ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ እና ሩዋንዳ እንደሚከናወን ነው የተገለጸው፡፡

ወጣቶቹ የሚያከናውኑት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር÷ ወንድማማችነትን፣ አንድነትን፣ ሰላምን፣ ትብብርን እና በጋራ መበልጸግን እንደሚወክል ተመላክቷል፡፡

ሦስተኛው ከሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ወጣቶች የሚሳተፋበት “የአፍሪካ ተስፋ የተጣለባቸው መሪዎች ስብሰባ” ሲሆን÷ በጥቅምት ወር ይካሄዳል ።

በዚህም ከሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ሁለት ሁለት ወጣቶች እንደሚውጣጡ እና ከቀድሞ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር ስለአህገራቸው እንደሚመክሩ ተጠቁሟል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ፍስሐ ሻወል በበኩላቸው÷ በርካታ አፋሪካውያን ኢትዮጵያን እንደእናታቸው እንደሚያዩ አንስተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ወዳጅነት በመሪዎች ደረጃ ብቻ እንደተወሰነ አስታውሰው÷ ዛሬ ይፋ የሆነው የትስስር ኩነት ግን ግንኙነቱን በወጣቶች፣ በምሁራን እና በቀድሞ መሪዎች ደረጃ ማስፋት የሚቻልበት ነው ብለዋል፡፡

አጋጣሚው ቀጣዩ ትውልድ ከአባቶቹ ጋር የተቋረጠበትን ክፍተት መሙያ፣ የትናንት ባለውለታዎቹን አውቆ ለአፍሪካ የተሻለ ብልጽግና እንዲሠራ ማነቃቂያ ጭምር መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ቢሆንም ይህንን የሀገራቱን ግንኙነት በወጣቶች ፣ በምሁራንና ሀገራቸውን ባገለገሉ የቀድሞ መሪዎች ደረጃ ለማድረግ ታስቦ ሲሠራ መቆየቱን ተመላክቷል፡፡

በፀጋዬ ወንድወሰን

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.