ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በመቀጠሌ ደስተኛ ነኝ – አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በመቀጠሌ ደስተኛ ነኝ ሲሉ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተናገሩ፡፡
አሰልጣኙ ባሳለፍነው ዓርብ ተጨማሪ የሁለት ዓመት ውል ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር መፈራረማቸውን ተከትሎ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አሰልጣኝ ውበቱ በመግለጫቸው÷ እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም በዋሊያዎቹ አሰልጣኝነት በሚቆየው ውል በወር የተጣራ 250 ሺህ ብር እንዲከፈላቸው ስምምነት መፈጸማቸውን አንስተዋል፡፡
ፌደሬሽኑ ባቀረበላቸው የውል ማራዘሚያ ደስተኛ መሆናቸውንም ነው አሰልጣኙ የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሃፊ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው ÷በተፈረመው ኮንትራት አሰልጣኙ ብሄራዊ ቡድኑን ለ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍና በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ከቀደሙት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ቅደሚያ የሚጠበቅባቸው ሃላፊነት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ የሚሰሩ ሌሎች የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱን ውል ለማራዘምም ከአሰልጣኞቹ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ባህሩ ተናግረዋል፡፡
በታሪኩ ጉታ