አደገኛ የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ በኡጋንዳ መቀስቀሱ ተሰማ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፈረንጆቹ 2019 ወዲህ በተላላፊነቱ አደገኛ ነው የተባለለት የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ በኡጋንዳ መቀስቀሱን የሀገሪቷ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ማክሰኞ ዕለት በኡጋንዳ ማዕከላዊ ሙቤንዴ አካባቢ በተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽን የ24 ዓመት ወጣት ሕይወት ማለፉም ነው የተነገረው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ፥ በኡጋንዳ ተከስቶ በማያውቅ የኢቦላ ቫይረስ ዝርያ የ24 ዓመት ወጣት መያዙ ተገልጿል፡፡
በወሩ በአካባቢው ሌሎች ሥድስት ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ የኡጋንዳ ፈጣን ምላሽ ቡድን ምርመራም አመላክቷል፡፡
የሰዎቹ ሕይወት ያለፈው በቫይረሱ ሳቢያ ሳይሆን እንዳልቀረም ነው የዓለም ጤና ድርጅት በመረጃው የጠቆመው፡፡
በቫይረሱ ተጠቅተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሌሎች ሥምንት ሰዎችም የሕክምና ክትትል ላይ መሆናቸውን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡