Fana: At a Speed of Life!

የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ከአውሮፓ የፓርላማ አባላት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የጤና ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ከአውሮፓ የፓርላማ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እየተካሄደ በሚገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ፣ በወቅታዊ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ÷የኢትዮጵያ መንግስት በሁለንተናዊ ዘርፎች በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና ሀገሪቱ እያጋጠማት ያለውን ችግር ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ያለውን ፍላጎት ወደኋላ በመተው አሸባሪው ህወሓት ያወጣውን ሕገመንግስት በመፃረር ጦርነቱን በራሱ ፍላጎት እንዳስጀመረውም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለአየር ንብረት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት በዓመቱ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ መትከል መቻሉን አፈ-ጉባኤው ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ በበኩላቸው÷ አሸባሪው ህወሓት በድጋሜ በከፈተው ጦርነት በአማራና በአፋር ክልሎች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን አብርራተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም አሸባሪው ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ የሚላከውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለጦርነት ማዋሉን እና የኢትዮጵያ መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።

አሸባሪው ህወሐት በከፈተው ጦርነት አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹ 5 ሺህ 567 ሴቶችና ህጻናት በመኖራቸው ለጤና፣ እና ሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲደረግላቸው እየተሰራ እንደሆነ መገለጹን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በጦርነቱ ሳቢያ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች እንደተፈናቀሉ እና በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በድርቅና በጎርፍ የተጎዱ ዜጎች በመኖራቸው የአውሮፓ ህብረት አስፈላጊውን የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንዲያደርግም ተጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝቦች ሰላም ወዳድ መሆናቸውን ያለውን እውነታ ለዓለም እንዲያሳውቁ ለአውሮፓ የፓርላማ አባላትን ጥሪ ቀርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.