Fana: At a Speed of Life!

“የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት ለፖለቲካዊ ፍላጎት ማስፈጸሚያነት የዋለ እና እውነታውን የካደ ነው” – ጄፍ ፒርስ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያወጣው ሪፖርት ለፖለቲካዊ ፍላጎት ማስፈጸሚያነት የዋለ እና እውነታውን የካደ መሆኑን የታሪክ ተመራማሪው ጄፍ ፒርስ አስታወቁ።

ጄፍ ፒርስ ካናዳዊው የታሪክ ተመራማሪ እና ደራሲ ሲሆኑ በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምርመራ ግኝት ላይ ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

ጄፍ ፒርስ በኮሚሽኑ በምስክርነት እና በመረጃ ምንጭነት የተጋበዙ ሰዎችን ጠቅሰው በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ÷ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተፈጽሟል ተብሎ በኮሚሽኑ የቀረበው ሪፖርት ለሽብር ቡድኑ ያደላ እና ኮሚሽኑ የጋበዛቸው የመረጃ ምንጮቹ ላይም መደናገርን የፈጠረ እንደሆነ አስፍረዋል፡፡

ተጋባዥ የመረጃ ምንጮቹ በምርመራ ሂደቱ ውስጥ ማስረጃ በመስጠት እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ቢጋብዛቸውም ዕማኝነታቸው በሪፖርቱ ውስጥ እንዳልተካተተ እንደገለጹላቸውም ጠቁመዋል።

ፍጹም የጥናትን መሥፈርት ያላሟላ መሆኑን እንደገለጹላቸውም ጠቅሰው፥ በምርመራ ሂደቱ ውስጥ ወደ ሚፈልጉት ሁነት ብቻ እየመሯቸው የፈለጉትን እንዲናገሩ ሲያደርጓቸው እንደነበር መናገራቸውን የታሪክ ተመራማሪው በጽሑፋቸው ገልጸዋል፡፡

ትግራይ እና አማራ ክልሎች ላይ ተፈጸሙ ያሏቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪዎቹ ኮሚሽኑ በፈለገው መንገድ ብቻ ማቅረባቸውንም ነው ጄፍ ፒርስ ዕማኞቹን ጠቅሰው የገለጹት።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ÷ በአፋር ክልል የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎችን ፣ በቤቶቻቸው ፣ በመስጂዶቻቸው ፣ በሐይማኖታዊ መፅሐፍት እና በአካባቢያቸው ላይ የተፈጸሙ የከባድ መሳሪያ ድብደባዎችን ሁሉ ለማካተት አለመፈለጉንም ጄፍ ፒርስ በጽሑፋቸው አስፍረዋል፡፡

በአፋር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በመንገድ እና በመጠለያ ጣቢያዎች ያዩት አበሳ፣ ውሃ ጥም እና የ42 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሃሩር ፀሐይ ቃጠሎ ኮሚሽኑ እንዳላየ ማለፉንና በምርመራው አለመዳሰሱንም ነው በፅሑፋቸው ያመላከቱት፡፡

በወቅቱ የተመድን እህል የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ተፈናቃዮቹን እያዩ አልፈዋቸው ወደ መቀሌ ያለምንም ችግር መሄዳቸውን አስታውሰው፥ በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥናት ውስጥ የተፈናቃዮቹ ሁኔታ በአንድ መስመር ብቻ ተድበስብሶ እንደታለፈም ጄፍ ፒርስ በፅሑፋቸው አውስተዋል፡፡

በሚገርም ሁኔታ በአፋር ክልል ባሉ የትግራይ ነዋሪዎች የክልሉ ልዩ ኃይል ጭፍጨፋ ፈፅሟል ፣ አግቷል ለማለት ግን በምርመራ መረጃው ከበቂ በላይ ቦታ እንዳላጡም አስረድተዋል፡፡

ይህም ኮሚሽኑ ጉዳዩን በተመለከተ ያወጣው ሪፖርት ለፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያነት እንዲውል በማቀድ ያወጣውና እውነታውን የካደ መሆኑንም ነው የሚገልጹት።

ጸሐፊው ÷ ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምርመራ ያካሄደው ለሰብዓዊነት ተቆርቁሮ እንዳልሆነና የተመድን የፖለቲካ አጀንዳ አቅርቦ ፍላጎቱን በድርጅቱ የጸጥታው ምክር ቤት በኩል ለማስፈጸም መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

ምንም እንኳን የተመድ አንድ ተቋም የሆነው የዓለም ጤና ድርጅት ከተቋቋመለት ዓላማ ውጪ የሆነ ኢ-ሥነ-ምግባራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እንዳይገባ መተዳደሪያ ደንቡ ቢያግደውም ዋና ዳይሬክተሩ ቴድሮስ አድኀኖም ግን በቀን እስከ 8 ጊዜ ስለ አሸባሪ ቡድኑ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን መረጃዎች እንደሚያጋራ ጄፍ ፒርስ በመረጃቸው አስፍረዋል፡፡

ዓላማቸው ከተመድ ጋር ስለሚናበብም ግለሰቡን ከመክሰስ እና ከስራ ከማገድ ይልቅ ሁኔታውን በዝምታ ሲመለከቱት እንደቆዩና እንደሚመለከቱትም ነው የገለጹት ጄፍ ፒርስ፡፡

ምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ የቆዩትን “አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሕጻናትን አስታጥቋል” የሚል መረጃ ኮሚሽኑ እንዳላካተተም ነው ጄፍ ፒርስ የገለጹት፡፡

አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ ሕዝባዊ ማዕበል መጠቀሙንም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ እንዳላካተተ ጠቁመዋል፡፡

70 በመቶ የሚሆነው የተመድ የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ እንዲደርስ መደረጉንም ያነሱት የታሪክ ተመራማሪው፥ አሸባሪው ህወሓት የሰብዓዊ አቅርቦቱን ጨምሮ 12 ቦቴ ነዳጅ ዘረፋ ሲፈፅም ኮሚሽኑ ሁኔታውን በሪፖርቱ አለሳልሶ ማለፉ እንዳስደነቃቸው ነው የገለጹት፡፡

ጄፍ ፒርስ ሁኔታዎችን በዝርዝር እና በማስረጃ ካብራሩም በኋላ ተመድ የሰብዓዊ መብቶችን ለፖለቲካ መጠቀሚያነት የሚያውል “የበሰበሰ ድርጅት” እንደሆነ በመደምደሚያቸው ላይ አመላክተዋል፡፡

“የዓለም ጤና ድርጅት በሥርዓት እና መመሪያ የማይገዛ የጦር ወንጀለኛ ቡድን አባል የሚመራው ትልቅ ዓለምአቀፋዊ ተቋም መሆኑን ነው የጻፉት፡፡

ኢትዮጵያ ከኒውዮርኩ ጠቅላላ ጉባዔ ፍትኀዊ ውሳኔ እንዳትጠብቅ ይልቁንም በአኅጉሪቱ በኢኮኖሚና ጸጥታ ላይ በጥምረት የሚሰራ ኅብረት ለመገንባት ከመቸውም ጊዜ በላይ የአፍሪካ ሀገራትን ማስተባበር እንዳለባት ምክረ-ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

በዓለማየሁ ገረመው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.