Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመስቀል በዓል እሴቱንና ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ህብረተሰቡ በትብብር እንዲሰራ ጠየቁ

 

 

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ደመራ እና የመስቀል በዓል እሴቱንና ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ህብረተሰቡ በትብብር እንዲሰራ ጠየቁ።

 

በአዲስ አበባ ከተማ ከመስቀል በዓል እና ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ህዝባዊ ውይይት ተደርጓል።

 

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓሉ ፀረ ሰላም ሃይሎች በጦርነት የደረሰባቸውን ኪሳራ በተላላኪዎቻቸው አማካኝነት አዲስ አበባ ላይ ለመመለስ ርብርብ በሚያደርጉበት ወቅት የሚከበር ነው ብለዋል።

 

እነዚህ ሃይሎች በዓለም ኢትዮጵያን ያስተዋወቁ በዓላት የስበት ማዕከል በመሆናቸው እንደ ትልቅ እድል ለመጠቀም እየሞከሩ መሆኑንም አንስተዋል።

 

ሆኖም ህዝቡ በየአካባቢው መፈናፈኛ እንዳሳጠቸው በመጥቀስ ክፍተት ካልተሰጣቸው ምንም አይነት መንገድ እንደሌላቸውም ነው የገለጹት።

 

“ጦርነቱን ዳግም የምናሸንፋቸው በዓሉን ሰላማዊና ደማቅ አድርገን በማክበር ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች እነዚህ ሴረኞች ምንም እድል አይኖራቸውም” ብለዋል ባስተላለፉት መልዕክት፡፡

 

“በእምነት በብሄር በአካባቢ እንደተከፋፈልን አስመስለው ለዓለም ማሳየት ለሚፈልጉ ሃይሎችም በዚህ በዓል አንድነታችንን ለዓለም እናሳያለን” ነው ያሉት።

 

የውይይቱ ተሳታፊዎች በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ እሴቱንና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር እንደተዘጋጁ መናገራቸውን የከንቲባ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.