Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ10 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 10 ፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ትናንት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ10 ሰዎች ህይዎት አለፈ።

አደጋው ከሰሜን ወሎ ዞን ላልይበላ ከተማ ወደ ግሸን ደብረከርቤ ይጓዝ የነበረ አውቶብስ ጥልቅ ገደል በመግባቱ የተከሰተ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ነፃነት አበራ እንደገለጹት፥ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ 23 ቀበሌ ልዩ ስሙ አጥቢያ በተባለ ቦታ ላይ ወደ ኋላ ተንሸራቶ ነው አደጋው የደረሰው።

በደረሰው አደጋም የ10 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፥ በ14 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

በአደጋው ጉዳት ያልደረሰባቸው መንገደኞች መኖራቸውን የተናገሩት ኮማንደር ነፃነት፥ ጉዳዩን በዝርዝር የሚያጣራ ቡድን ወደ ቦታው ማምራቱን ጠቁመዋል።

የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ተወስደው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑም ተገልጿል።

በሰላም አሰፋ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.