Fana: At a Speed of Life!

የመስቀል በዓል አብሮነትን በአደባባይ በማንጸባረቅ ረገድ የጎላ ማኅበራዊ ፋይዳ አለው – አቶ አሻድሊ ሐሰን

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 16 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር አብሮነትን በአደባባይ በማንጸባረቅ ረገድ የጎላ ማኅበራዊ ፋይዳ አለው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ገለጹ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ፥ የመስቀል በዓል ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያስተዋውቁ ኃይማኖታዊ በዓላት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር አብሮነትን በአደባባይ በማንጸባረቅ ረገድ የጎላ ማኅበራዊ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል።

የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ ለሃገር ሠላም በመጸለይ፣ በመረዳዳትና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል።

በተጨማሪም ህዝቡ በዓሉ በሠላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የዘንድሮው የመስቀል በዓል ሀገራችን በአሸባሪው ህወሓት የተከፈተባትን ጦርነት እየተከላከለች ባለችበት ወቅት የሚከበር መሆኑን የጠቆሙት አቶ አሻድሊ ፥ ለሀገር ሠላም መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ማጠናከር ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

አክለውም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የ2015 የመስቀል በዓል የሠላም፣ የፍቅር፣ የደስታና የአብሮነት በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘውም በክልሉ ለሚከበረው የሽናሻ ብሄር ዘመን መለወጫ “ጋሪ- ወሮ ” እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

በዓሉ የሰላም፣ የአንድነትና የብልጽግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.