Fana: At a Speed of Life!

ከፍተኛ ባለስልጣናት በዝነኛው ከያኒ ማዲንጎ አፈወርቅ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በዝነኛው ከያኒ ማዲንጎ አፈወርቅ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ በአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ሐዘን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡ ዶክተር አብርሃም በላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ሀገሩንና ሕዝቡን ወዳድ፣ እጅግ ተወዳጅና በሥራዎቹ ታዋቂ የነበረው የጥበብ ሰው ማዲንጎ አፈወርቅን ሕልፈት ለማመንና ለመቀበል የሚከብድ ነው ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፥ “ሥራዎችህ ጀግኖችን አጀግነዋል፤ የሀገር ፍቅርን ሰብከዋል፤ የሚሊዮኖችን ቀልብ ገዝተዋል” ሲሉ ለአርቲስቱ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።

የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ÷ በድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ሕልፈት ሐዘን እንደተሰማቸው ገልጸው÷ ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

በተመሳሳይ ዶክተር ይልቃል ከፋለ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ለሀገሩና ለትውልድ ጥበብንና ባህልን አውርሶ ያለፈ እውቅ ከያኒ መሆኑን ገልጸው÷ የሚችለውን ሁሉ ለሚወዳት ሀገሩ ተቀኝቷል ብለዋል፡፡

በችግር ውስጥ ሆኖም ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር ሲል ከጠላት ጋር የሚዋደቀውን ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችንን እና የጸጥታ ኃይላችንን ግንባር ድረስ ዘልቆ አበረታትቷል ነው ያሉት።

ስለኢትዮጵያ ቀደምት ስልጣኔና ታሪክ፣ ሰላምና አንድነት፣ ነጻነትና ክብር በርካታ የጥበብ ሥራዎችን መሥራቱን ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ በአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ሕልፈተ ሕይወት ከልብ አዝኛለሁ ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ÷ ተወዳጁ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ማረፉን ስሰማ እጅግ ከባድ ሐዘን ተሰምቶኛል፤ አርቲስቱ ሀገሩን የሚወድና ለሀገሩ ሠለቸኝ ደከመኝ ሳይል በጽናት ብዙ የሠራ ነው ብለዋል፡፡

ባለስጣናቱ ለአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና ለጥበብ አድናቂዎቹ በሙሉ መጽናናትን ተመኝተው÷ ፈጣሪ የአርቲስቱን ነፍስ በአጸደ ገነት ያኑር ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.