Fana: At a Speed of Life!

ከ97 ኪሎ ግራም በላይ ኮኬይን ተያዘ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ97 ኪሎግራም በላይ የሚመዝን ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ እጽ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተያዘ።
 
መነሻዋን ከናይሮቢ ኬንያ መዳረሻዋን አዲስ አበባ ያደረገች ግለሰብ 97 ነጥብ 48 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮኬይን በያዘቻቸው ሁለት ሻንጣዎች ውስጥ ለማሳለፍ ስትሞክር በጉምሩክ ኮሚሽን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርንጫፍ በቁጥጥር ስር ውላለች፡፡
 
ተጠርጣሪዋ የትራንዚት መንገደኞች እና ቀረጥና ታክስ የሚከፈልበትን እቃ ያልያዙ መንገደኞች የሚወጡበትን በዝቅተኛ የስጋት ደረጃ ወይም አረንጓዴ የጉምሩክ ማለፊያ መስመር በመጠቀም እያንዳንዳቸው 48 ነጥብ 62 እና 48 ነጥብ 86 ኪሎግራም ክብደት ያላቸውን ሁለት ሻንጣዎችን ለማሳለፍ ስትሞክር በቁጥጥር ስር ውላለች፡፡
 
ግለሰቧ በያዘቻቸው ሻንጣዎች ውስጥ የሚገኙት እቃዎች በመፈተሻ መሳሪያ እንዳይለዩ ለማድረግ መጽሐፍ በማስመሰል እና በአሉሙኒዬም ፎይል በመጥቅለል ለመደበቅ የሞከረች ቢሆንም በተደረገው ጥብቅ ፍተሻ እና ክትትል በሻንጣዎቹ ውስጥ ያለው ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ እጽ መሆኑ ሊረጋገጥ ችሏል፡፡
 
አደንዛዥ እፁ ፍተሻውን አልፎ ቢገባ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ከማስከተሉ በተጨማሪ ለሽብርተኞች ቢተላለፍ የዜጎችን ደህንነት የማናጋት አቅሙ ከፍተኛ እንደሆነ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቋል።
 
የግለሰቧን እንቅስቃሴ በንቃት ሲከታተሉ ለነበሩ በጉምሩክ ኮሚሽን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርንጫፍ ሰራተኞችና አመራሮች፣ አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ለተሳተፉ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት ሰራተኞች ፣ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዲቪዥን እና ለፀረ- አደንዛዥ ዕፅ ግብረ ሃይል ጉምሩክ ኮሚሽን ምስጋና አቅርቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.