Fana: At a Speed of Life!

የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ በደመቀ መልኩ በአዲስ አበባ ከዛሬ ጀምሮ እየተከበረ ነው- ዶ/ር ሂሩት ካሳው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ በደመቀ መልኩ በአዲስ አበባ ከዛሬ ጀምሮ እየተከበረ መሆኑን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ፡፡
 
የቢሮው ሃላፊ ሃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በሰጡት መግለጫ ÷በዓሉ እሴቱን ጠብቆ በሰላምና በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር የከተማ አስተዳደሩ ሰፊ ዝግጅቶች እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
 
ዛሬ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች የፓናል ውይይት መካሄዱን የገለጹት ዶ/ር ሂሩት÷ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ አልባሳት፣ ጌጣጌጥና ምግቦችን ጨምሮ የበዓሉን ግብዓቶች ማህበረሰቡ በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያስችል ባዛር መከፈቱንም ተናግረዋል።
 
በነገውም ዕለት በሁሉም ክፍለ ከተሞች የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ጠቁመው ÷ ዓርብ ደግሞ እንደ ከተማ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመተባበር የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ አመላክተዋል፡፡
 
በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚገቡ እንግዶችን ለመቀበል በአምስቱም የከተማዋ መውጫ በሮች ዝግጅት መደረጉን አንስተው÷ ይህም የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
 
የኢሬቻ በዓል ማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ሂሩት÷ የከተማዋ ነዋሪም በተለመደው የእንግዳ አቀባበል ባህል መሰረት የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌት የሆነውን በዓል ማክበር ይገባል ብለዋል።
 
ኢሬቻ በዓለም የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት የተመዘገበው የገዳ ስርዓት አካል መሆኑን በመገንዘብ እሴቱን ጠብቆ በደመቀ ሁኔታ ይከበራልም ነው ያሉት።
 
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል “ኢሬቻ ለሰላምና ለወንድማማችነት ” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር መጠቆማቸውንም ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.