Fana: At a Speed of Life!

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ከኔዘርላንድስ አምባሳደርና በአፍሪካ ህብረት፣ በኢጋድና ዩኔካ  ቋሚ ተወካይ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ  በኢትዮጵያ ከኔዘርላንድስ አምባሳደርና በአፍሪካ ህብረት፣ በኢጋድና ዩኔካ  ቋሚ ተወካይ ጃን ቤከር ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ÷ በመጋቢት 2023 በኒውዮርክ በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት የውሃ-የኮንፈረንስ ላይ ኢትዮጵያ የምታቀርበው የድጋፍ ፍላጎትና በአኩዋፎርኦል የተባለውና በውሃ ላይ የሚሰራ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ባቀረበው የውሃ ፋይናንስ አሰራር ላይ ያተኮረ ነው።

የውሃ-ኮንፈረንሱን  በተመለከተ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሃብታሙ ÷ በሚኒስቴሩ የ10 ዓመታት እስትራቴጂክ እቅድ ውስጥ የተካተቱትን ቁልፍ የስራ አፈጻጸም አመልካቾችን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ የገባችውን ቃል በመንግስታቱ ድርጅት የውሃ ኮንፈረንስ እንደምታቀርብ አመላክተዋል።

በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ላይ የሚደረጉ ጥረቶች በኮንፈረንሱ እንደሚንፀባረቁ የገለጹ ሲሆን÷ በኮንፈረንሱ የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭን ጨምሮ ዘላቂ የውሃ ሃብት አስተዳደርና ልማት ውጥኖች እንደሚነሱም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የአኳፎርኦል ማኔጂንግ ዳይሬክተር  ጆዚን ስሉጂስ÷በመድረኩ በግል የፋይናንስ ተቋማት የውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጄክቶችን በገንዘብ መደገፍ  ላይ ትኩረት ያደረገ ገለፃ አድርገዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላም  በቀረበው ሀሳብ ላይ ተወያይቶ የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ  ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የበላይ አመራሮችና እና ከኔዘርላንድስ ኢምባሲ የተውጣጣ ግብረ ሃይል ለማቋቋም መግባባት ላይ መደረሱን ከውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.