Fana: At a Speed of Life!

አንዳችን የአንዳችን ጠባቂዎች በመሆን የኮሮና ቫይረስን መከላከል ይገባናል – ጠ/ሚ ፅህፈት ቤት

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 10 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አንዳችን የአንዳችን ጠባቂዎች በመሆን የኮሮና ቫይረስን መከላከል እንደሚገባ ገለጸ።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ፅህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በመግለጫውም ቫይረሱ ከየትኛውም ሀገር ወይም ዜግነት ጋር የተያያዘ አለመሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ በመጥቀስ፥ ሰው የሆነ ሁሉ ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆኑን አንስቷል።

መግለጫው በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ በሚገኙ የውጭ ሃገር ዜጎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል የሚል መረጃ የተለያዩ ሃገራት ኤምባሲዎች ማውጣታቸውን ተከትሎ የተሰጠ ነው።

ፅህፈት ቤቱ በመግለጫው ቫይረሱን ለመከላከል የጤና ሚኒስቴር ያወጣውን የመከላከል እና ጥንቃቄ መመሪያ መከተል እንደሚገባም አስገንዝቧል።

በመሆኑም ቫይረሱን የመከላከል ጥረታችን ሰብአዊነታችንን የሚጋርድ እና ርኅራሄን የሚያስጥል መሆን አይኖርበትምም ነው ያለው።

አያይዞም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አካል እንደ መሆናችን መጠን አንዳችን የአንዳችን ጠባቂዎች በመሆን ቫይረሱን መከላከል ይገባልም ብሏል።

ከዚህ ባለፈም የበሽታ ፍርሃት ሰብአዊነታችንን እንዲነጥቀን አንፍቀድ ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.