Fana: At a Speed of Life!

በባህርዳር ከተማ ከ20 ሺህ በላይ ሀሰተኛ ዶላር መያዙ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 20 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህርዳር ከተማ 20 ሺህ 600 ሀሰተኛ ዶላር በህገወጥ መንገድ ለምንዛሬ ሊውል ሲል ከእነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
መነሻቸውን ደሴ ያደረጉት የሃሰተኛ ዶላር አዘዋዋሪዎቹ ባህርዳር ከተማ ሲደርሱ በልዩ ኃይል የክትትል አባል መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ሌሎች ግብረ አበሮችን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን በባህርዳር ከተማ የ5ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አበዙ ትኩየ ተናግረዋል፡፡
ገንዘቡ ሀሰተኛ ስለመሆኑ በባንክ ባለሙያዎች መረጋገጡን ምክትል ኢንስፔክተር አበዙ መግለጻቸውን የአማራ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።
የ5ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ዘሪሁን አስራደ በበኩላቸው ሃሰተኛ ዶላሩ ወደ ገበያ ቢገባ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ ሊያደርስ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ ይህን መሠል እና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶችን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን ሊሰራ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.