Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያየዘ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 216 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 216 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፥ የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገሪቱ መግባቱን ተከትሎ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉን ተናግረዋል።

ለዚህም ከክልል ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ችግሩን የሚከታተሉ ግብረ ሃይሎች መቋቋማቸውን ነው የገለጹት።

የክልሉ ከተሞች ላይ በተካሄደ ጥናትና አሰሳ ጤፍ 10 በመቶና በርበሬ 33 በመቶ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው ምርቶች መሆናቸው ተመላክቷል።

በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችና መድሃኒቶች ላይም ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሪ መደረጉን ሃላፊዋ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ግርግሩን በመጠቀም በምርቶች ላይ ባዕድ ነገሮችን ቀላቅሎ የመሸጥ፣ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶችን ለገበያ የማቅረብ እና ሚዛን የማጓደል ህገ ወጥ ተግባራት ታይተዋል ነው ያሉት።

በዚህም መሰረት ሀዋሳን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች በሚገኙ 149 የንግድ ሱቆች፣ 49 የእህል በረንዳዎችና ወፍጮ ቤቶች፣ 7 ፋርማሲዎች፣ 6 የምግብና መጠጥ ቤቶች፣ 6 ነዳጅ ማደያዎች እና 6 ግለሰቦች በድምሩ በ216 የንግድ ተቋማት ላይ አስተማሪ የሆኑ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ቀለል ያሉ ወንጀሎችን በሰሩ ድርጅቶች ላይ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በዚህ የችግር ወቅት ያለአግባብ ለመጠቀም መሞከር ከሰብኣዊነት መውጣት ነው ያሉት ወይዘሮ ሂክማ፥ ህዝቡ በመደጋገፍና በመተሳሰብ መንፈስ ይህን አስቸጋሪ ወቅት ሊሻገረው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ማህበረሰብም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና ከአጋላጭ ሁኔታዎች እንዲርቅ ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የመድሃኒት አቅርቦትና የመገልገያ ቁሳቁሶችን በሚመለከትም ከመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.