Fana: At a Speed of Life!

የግሸን ደብረ ከርቤ በዓልን እና አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግሸን ደብረ ከርቤ በዓልን እና የአካባቢውን ሐብቶች በማልማት የቱሪስት መዳረሻና ዘላቂ የገቢ ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት ሥፍራ የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግሥ በዓል በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ዛሬ በድምቀት ተከብሯል።

የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያም በዓሉ በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን  አስታውቋል።

የክልሉ የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ÷ በክልሉ ለቱሪዝም መስህብነት የሚውሉ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ የተፈጥሮ ፀጋዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

እነዚህን የመስህብ ሐብቶች በማጥናት፣ በመለየትና በማልማት እንዲሁም ተገቢውን የማስተዋወቅ ሥራ በመስራት ኅብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በየዓመቱ የሚከበረውን የግሸን ደብረ ከርቤ በዓልና በአካባቢው ያለውን የመስህብ ሐብት በአግባቡ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በማሟላት የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም እንደሚሰራም ነው አቶ ጣሂር የጠቆሙት።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.