Fana: At a Speed of Life!

የኢስታንቡል ነጻ የንግድ ቀጠና ከድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ጋር ትስስር መፍጠር እንደሚፈልግ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢስታንቡል ነጻ የንግድ ቀጠና ከድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ጋር በጋራ ለመሥራት እና ትስስር ለመፍጠር ያለውን ፍላጎት ገለፀ፡፡

ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የተውጣጣ ልዑክ በቱርክ የሚገኘውን የኢስታንቡል ነጻ የንግድ ቀጠናን ጎብኝቷል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አዲሱ ማሞ የተመራው ልዑክ÷ ከኢስታንቡል ነጻ የንግድ ቀጠና ዋና ዳይሬክተር፣ ምክትል ኃላፊ እና የቱርክ ንግድ ሚኒስቴር ኮንሱለር ጋር በጋራ መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡

የኢስታንቡል ነጻ የንግድ ቀጠና ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ ስለ ነጻ ንግድ ቀጠናው በሰጡት ማብራሪያ÷ በዋናነት በፀሐይ ኃይል፣ በአውቶሞቲቭ አቅርቦት ኢንዱስትሪ፣ በባሕር ተሽከርካሪ ክፍሎች፣ በማሽነሪ ኢንዱስትሪ እና በማሽን መሳሪያዎች፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ በኬሚካል፣ በጨርቃጨርቅ እና በኮስሞቲክስ ዘርፎች ላይ የተለያዩ ኩባንያዎች በሥራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

አቶ አዲሱ ማሞ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ስላሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት የንግድና የሎጅስቲክስ ዕድሎች ገለጻ አድርገዋል፡፡

በቀጣይ በጋራ መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መደረሱን የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢስታንቡል ነጻ የንግድ ቀጠና በቱርክ የመጀመሪያው እና ግምባር ቀደሙ ሲሆን÷ በ1994 ዓ.ም የተመሰረተ እና ከ26 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው አጠቃላይ የንግድ ልውውጡም 90 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት በነጻ ንግድ ቀጠናው ውስጥ ከ300 በላይ ኩባንያዎች እና ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.