Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሕብረት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመግታት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) አስታወቀ።

ማዕከሉ ትናንት በሰጠው መግለጫ ኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ እስካሁን በአፍሪካ የ16 ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ፤ ከ640 በላይ ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ መያዛቸውን ይፋ አድርጓል።

የአፍሪካ ሲዲሲ ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ኒኬንጋሶንግ እንዳሉት፥ በዓለም ላይ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 ሲጠቁ፥ ከእነዚህ ውስጥ ከ640 በላይ የሚሆኑት በ34 የአፍሪካ ሃገራት ይገኛሉ።

ከሀገራቱ መካከል ግብጽ 210፣ ደቡብ አፍሪካ 116፣ አልጀሪያ 72፣ ሞሮኮ 54፣ ሴኔጋል 36 ተጠቂዎችን ይዘዋል።

የሟቾችን መረጃ በተመለከተም በአልጀሪያ፣ ግብፅ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋልና ካሜሩን በአጠቃላይ 16 ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን ይፋ አድርገዋል።

በሌላ በኩል 41 ህሙማን ከበሽታው ማገገማቸውን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም የአፍሪካ ሕብረት በአባል ሀገራቱ ስለ በሽታው ወቅታዊ መረጃ ልውውጥና በየሀገሩ ለሚገኙ የፀረ ኮሮናቫይረስ ግብረ ሃይላት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አፍሪካ ሲዲሲ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎችን ለመመርመር የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ማሰራጨቱን፣ 41 ሀገራት የመመርመር አቅም ማጎልበታቸው፤ የምርመራ መሳሪያ (ኪት) አቅርቦት ማሟላታቸውንና ማዕከሉ ተጨማሪ የምርመራ መሳሪያ ግዥ ፈጽሞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል እንደሚያሰራጭም አስታውቋል።

ለባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን፣ የማዕከሉ ሰራተኞችን በሽታው በበረታባቸው እንደ አልጄሪያና ሴኔጋል አይነት ሀገራት ውስጥ ማሰማራቱንና እስከ አሁን ለአባል ሀገራቱ ምላሽ የሚሰጡ 24 በጎ ፈቃደኞችን መመልመሉን ገልጸው፤ ወደፊትም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ከሲዲሲ በተጨማሪ እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት የበሽታውን መዛመት ለመግታት በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን የቻይና መንግስት 2 ሺህ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ቁሳቁሶችን ለሲዲሲ ሲያበረክት፣ በሽታውን በመግታት ያላትን ተሞክሮ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የእውቀት ስራ አመራር ድጋፍ ማድረጓን ጠቅሰዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም እጅን አዘውትሮ መታጠብ፣ ከሰዎች ጋር ያለውን ቅርርብ መቀነስ፣ የበሽታው ምልክቶች ሲስተዋሉ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ፣ ሳልና ማስነጠስ ሲከሰት ወደሌሎች ላለማስተላለፍ ጥንቃቄ ማድረግና ሌሎች መንስኤ ከሚሆኑ ድርጊቶች በመቆጠብ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.