Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ አስተዳደር ባለፉት 3 ወራት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በተቀናጀ መንገድ ማከናወኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ሦስት ወራት በተደራጀ የሕዝብ ተሳትፎ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በተቀናጀና በተዋሀደ መንገድ ማከናወኑ ተገለጸ፡፡

አስተዳደሩ ባለፉት ሦስት ወራት የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎችና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከከተማ እስከ ወረዳ ካሉ አመራሮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱም ባለፉት ሦስት ወራት አመራሩ በትብብርና በቅንጅት ተደራራቢ ተግባራትን ማሳካት መቻሉን እና ውጤት ማስመዝገቡ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ማጠቃለያ እንደተናገሩት÷ ከሁሉ በላይ በተደራጀና በተናበበ ሁኔታ ከመራን ሥራዎቻችን ስኬታማ እንደሚሆኑ ልምድ የወሰድንበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡

የአመራሩ ግንኙነት ጤናማ ከሆነ በሕዝብ ውስጥ ያለው ሁኔታ ጤናማ እንደሚሆን አይተናልም ነው ያሉት፡፡

አስተዳደሩ በክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች በምገባና ማዕድ ማጋራት በመሳሰሉ ሥራዎች ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ከአስተዳደር ወሰን ማካለል ጋር በተያያዘ የተሠሩ ሥራዎች የሕዝቦችን ዘላቂ ግንኙነት በሚያጠናክር መልኩ መከናወናቸውን ጠቁመው÷ የተሠሩት ሥራዎች ለዘላቂ ሰላማችን እጅግ ጠቃሚ እንደነበሩ አንስተዋል።

አሸባሪዎች በከተማዋ የኢኮኖሚ አንድ ግንባር በመፍጠር የኑሮ ውድነቱን ለማባባስ ያደረጉት ጥረት መክሸፉን የገለጹት ከንቲባ አዳነች÷ በርካታ ምርቶችን ወደ ከተማዋ በማስገባት የተሠራው ሥራ በጥንካሬ የሚነሳ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የተቋም ግንባታ ሥራ፣ የተደራጀ የሕዝብ ተሳትፎ ማጠናከር፣ የተጠያቂነትን ስርዓት ማስፈን (የፖለቲካ ተጠያቂነት ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ተጠያቂነት ማስፈን ያስፈልጋል)፣ በቅንጅት መሥራት፣ የሥራ ባህል ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው÷ አጠቃላይ ትምህርት የሚወሰድባቸውና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

አገልግሎት ከእጅ መንሻ ነፃ መሆን እንዳለበት አሳስበው÷ የጠላትን ዕቅድ ማፈራረስ የቻለ አመራር አገልግሎትን ነፃ ማድረግ እንደማይሳነውም አስገንዝበዋል፡፡

ዲጂታላይዜሽን፣ የሕግ የበላይነትና ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ መለሰ አለሙ እንደገለጹት አሁንም ቢሆን የሕዝቡ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄ ፍላጎት ጊዜ የሚሰጥ ባለመሆኑ÷ የስኬት ግምገማችን ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም መሆን አለበት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው÷ የአመራሩ የሥራ ባህልና ተቋም ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ኅብረት ያለው እና ለውጤት የሚተጋ አመራር በመኖሩ ብዙ ችግሮችን አልፈናል ብለዋል፡፡

ነዋሪው በዓል ሲመጣ መጣልኝ ብሎ የሚደሰትበት እንጂ መጣብኝ ብሎ የሚጨነቅበት እንዳይሆን መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.