Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ጠባብ ቤት ውስጥ 150 ሆነው ሺሻ ሲያጨሱ የተገኙ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ በአንድ ጠባብ የቀበሌ ቤት ውስጥ ታጭቀው ሺሻ ሲያጨሱ የተገኙ 150 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገለፀ።

የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው ሰፊ ጥረት ስጋቱን ችላ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች ሺሻ የማስጨስ እና ጫት የማስቃም ህገ ወጥ ተግባራቸውን ቀጥለውበታል ብሏል የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መረጃ።

ይህ ተግባር ከህገ ወጥነትም ባለፈ በሀገሪቷ የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር እየተደረገ ላለው ጥረት ሌላ እንቅፋት እንደሚሆን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ከበደ አስፋው ገልፀዋል።

የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ከደንብ ማስከበር አገልግሎት ፅህፈት ቤት ጋር በመተባበር ባደረጉት ቁጥጥር በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ጎማ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ጠባብ የቀበሌ ቤት ውስጥ 150 ሰዎች ተሰብስበው ሺሻ ሲያጨሱ እና ጫት ሲቅሙ አግኝቶ በቁጥጥር ስር በማዋል እርምጃ እንዲወሰድባቸው አድርጓል ብለዋል።

በተመሳሳይ የቀበሌ ቤቱን ከሌላ ግለሰብ ተከራይተው ህገ ወጥ ተግባሩ እንዲፈፀም ያመቻቹ ግለሰቦችም እርምጃ እንደተወሰደባቸው ኮማንደር ከበደ አስፋው ተናግረዋል።

በተለያዩ ጊዜያት መሰል ህገ ወጥ ተግባራት ሲፈጽሙ ከደንብ ማስከበር ጋር በመሆን አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ ሲወስዱ እንደቆዩ ያስታወሱት ሃላፊው በህገ ወጥ ጫት ማስቃሚያ እና ሺሻ ማስጨሻ ቤቶች ላይ የሚወስዱትን ህጋዊ እርምጃ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.