Fana: At a Speed of Life!

የተጎዱ ወገኖችን ለማገዝ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተጎዱ ወገኖችን ለማገዝ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሳተፉ በደቡብ አፍሪካ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር ጥሪ አቀረቡ፡፡

አምባሳደሩ በደቡብ እና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ለ3ኛ ጊዜ በሽብርተኛው የህወሓት ቡድን የተከፈተውን ጥቃት ተከትሎ በሀገር ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ እንዲሁም የህዝብን ሰላም ለማረጋገጥ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አምባሳደር ሙክታር አንስተዋል፡፡

በተለይም በሽብር ቡድኑ ጥቃት የተፈናቀሉ ወገኖች ከሞቀ ጎጇቸው ወጥተው ለችግር መጋለጣቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በዚህም ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በደቡባዊ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት የድጋፍ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን በተደረገው ጥረትም ኢትዮጵያውያን የሚያኮራ ምላሽ እየሰጡ እንደሆነ ገልጸው ፥ ድጋፍ ማሰባሰቡ ጥሩ ውጤት እንደተገኘበትም ነው የተናገሩት፡፡

በደቡብ አፍሪካና ሚሲዮኑ በሚሸፍናቸው ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ንቅናቄውን በመቀላቀል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም ወገኖች ላይ ከደረሰው ጉዳት አኳያ ሲታይ ገና ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ አፈጻጸም እንዳለም ነው ያነሱት፡፡

እነዚህ ዜጎችን ወደነበረው ህይወታቸው ለመመለስ በርካታ የሃብት ማሰባሰብ ስራ እንደሚያስፈልግ ገልጸውም ፥ ወገኖች እያደረጉ ለሚገኙት ርብርብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የተቀሩ የሃብት ማሰባሰብ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ሚሲዮኑ ሰፋፊ እቅዶችን ይዞ መላው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲያሳትፉ ወደ ስምሪት ተገብቷልም ነው ያሉት፡፡

ይህን ጥሪ የሰሙ ወገኖችም ለሀገራዊ ጥሪው በንቃት እንዲሳተፉ መጠየቃቸውን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.