Fana: At a Speed of Life!

ቤተክርስቲያኗ መንፈሣዊ የስብከተ ወንጌል ጉባኤያትና የመንፈሳዊ ጉዞ መርሐ ግብሮች ለጥቂት ቀናት እንዲቆሙ ውሳኔ አሳለፈች

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሣዊ የስብከተ ወንጌል ጉባኤያትና የመንፈሳዊ ጉዞ መርሐ ግብሮች ለጥቂት ቀናት እንዲቆሙ ውሳኔ አሳለፈች።

በብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቋሚ ሲኖዶስ ያሳለፈውን ውሳኔ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጸሎትና ምሕላ አጠናክሮ ከማድረግ በተጨማሪ ጤነኞችን የመጠበቅ፣ ሕሙማን የመንከባከብና የማጽናናት ኃላፊነት ስላለባት ቋሚ ሲኖዶስ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ውሳኔዎች አሳልፏል ተብሏል።

በመግለጫቸውም በቅዳሴና በምሕላ ጸሎት ጊዜ በውስጥም ሆነ በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ዘርዘር ብሎ በመቆም መንፈሳዊ አገልግሎቶችን እንዲፈጸሙ ቤተክርሲያኗ መሳሰቧን ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ተናግረዋል።

ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና ጋር የማይጋጩ የመከላከያ መንገዶች ማለትም የእጅ ለእጅ መጨባበጥን ማቆም፣ እጅን በሚገባ መታጠብ፣ ሳይጠጋጉ ዘርዘር ብሎ መቆም፣ በመሳልና በማስነጠስ ጊዜ መጠንቀቅ፣ በመሳሳም ምትክ እማሄ ወይም ሰላምታ መስጠት በየአጥቢያው፣ በየገዳማቱና በያለንበት ሁሉ ተግባራዊ እንዲደረግ ነው ውሳኔ የተላለፈው።

ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ከተሳሳቱ መረጃዎች ተቆጥበው ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ መመሪያዎችን በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑና አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንደፈጽሙም ቤተክርስቲያኗ ማሳሰቧን ከቤተክርስቲያኗ ቴሌቪዥን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለራስና ለወገን በመቆርቆርና በመተዛዘን፣ አረጋውያንን በመጠበቅ፣ ነዳያን በማሰብ የበሽታውን ሥርጭት ተባብረን ማስቆም እንደሚገባ ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑ ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.