Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከ20 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ እና ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ መሀል የሚገነቡ ከ20 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በይፋ ተጀመረ።
ምክትል ከንቲባውን ጨምሮ፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ አካባቢዎች በተገኙበት የለገሃር አካባቢ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጀምሯል።
 
ኢንጅነር ታከለ ኡማ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ከዚህ ቀደም በቤቶች ግንባታ የነበሩ ክፍተቶች እንዳማይኖሩ እና መንግስት በቤቶች ግንባታ ከመቆጣጠርና ማስተዳደር ውጭ ሃላፊነት እንደማይኖረው ገልፀዋል።
 
የከተማ አስተዳደሩ 150 ሺህ በላይ ቤቶች የሚገነባ ሲሆን፥ በግሉ ዘርፍ ግን በርካታ ቤቶች ለማስገነባት መንግስት ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።
 
በቀጣይ በከተማ ነዋሪ የሚነሱ የቤት፣ የትራንስፖርት እና የስራ እድል ፈጠራ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል።
 
የአዲስ አበባ ከተማን ለመለወጥ እየተሰራ ያለውን ስራ የመዲናዋ ነዋሪዎች በጋራ በመቆም ሊደግፉ ይገባል ብለዋል።
 
የለገሃር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በ4 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን 10 ብሎኮች እና 1 ሺህ 680 መኖሪያ ቤቶች እንደሚኖሩት ተነግሯል።
 
ግንባታው በ10 ረቋራጮች የሚከናወን ሲሆን፥ ለ3 ሺህ ሰዎች ስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
 
ከሂልተን ጀርባ በልማት ምክንያት የሚነሱ ዜጎች በለገሃሩ የጋራ መኖሪያ ቤት እንደሚመደቡ ተናግረዋል።
 
አዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለሟሟላት የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ሳይቶች ተጀምረው በግንባታ ላይ የሚገኙትን ቤቶች በፍጥነት ለማጠናቀቅ እና በተያዘው በጀት ዓመትም 500 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ የግንባታ አማራጮች ለማስገንባት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።
 
በተያዘው በጀት ዓመትም በመልሶ ማልማት እና በአዳዲስ ፕሮጀክቶች በዘጠኙም ክፍለ ከተሞች በ69 ነጥብ 2 ሄክታ መሬት ከ20 ሺህ 504 በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ የማስጀመሪያ ስነ ስዓት እየተካሄደ ነው።
 
የቤቶቹ ግንባታ ወጪም በከተማ አስተዳደሩ እና በባንክ ብድር የሚሸፈን ይሆናል።
 
በእቅድ ከተያዙት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ስራ በ1 ሺህ 740 በጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራት ለ52 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጠር ይጠበቃል፡፡
 
ከጉለሌ ክፍለ ከተማ በስተቀር በሌሎቹ ዘጠኙ ክፍለ ከተሞች በመልሶ ማልማት እና በአዳዲስ ፕሮጀክት የመሬት ዝግጅት ከወዲሁ የተደረገ ሲሆን፥ እነዚህ ቤቶች ሲጠናቀቁ ከ102 ሺህ 520 በላይ ነዋሪዎችን ያስተናግዳሉ
ተብሎ እንደሚጠበቅ የከተማዋ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
 
ቤቶቹ በ20/80 እና በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም የሚገነቡ ሲሆኑ የቤቶቹን ግንባታ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚያደርግ ተጠቅሷል።
 
 
ለይኩን አለም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.