Fana: At a Speed of Life!

የኮንዶሚኒየም ዕጣ በማጭበርበር ተከሰው ነገር ግን ያልተያዙ ግለሰቦች ተይዘው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ14ኛ ዙር 20/80 እና ከ3ኛ ዙር 40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ የሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸውና ፍርድ ቤት ያልቀረቡ 10ኛ እና 11ኛ ተከሳሾች ተይዘው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡

ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ የሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው 9 ተከሳሾች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ሀላፊ የነበሩት ሙሉቀን ሀብቱ ምሩፅን ጨምሮ 9 ተከሳሾች ናቸው ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት።

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ያልተያዙ ተከሳሾችን ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርብ እና ክሱ ለተከሳሾቹ በንባብ ለማሰማት ነበር።

ነገር ግን ያልተያዙት 10ኛ እና 11ኛ ተከሳሾችን ፖሊስ ይዞ ባለማቅረቡ ክሱን በንባብ ማሰማት አልተቻለም።

የተከሳሽ ጠበቆችም ሁለቱ ተከሳሾች ባለመያዛቸው በእስር ላይ የሚገኙት ዘጠኙ ተከሳሾች ጉዳይ ከዚህ በላይ መራዘም የለበትም ለብቻው ሊታይ ይገባል የሚል ሀሳብ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል።

አቃቢ ህግ በበኩሉ የአስራ አንዱም ተከሳሾች የቀረበባቸው ክስ ተያያዥ በመሆኑ ማስረጃዎችም ተያያዥ በመሆናቸው ክሳቸው በአንድ ላይ መታየት ይኖርበታል የሚል መልስ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ የሙስና ወንጀል ችሎትም የግራ ቀኙን ሀሳብ ካደመጠ በኋላ ትእዛዝ ሰጥቷል።

በዚህም ያልተያዙት ሁለቱ ተከሳሾችን ፖሊስ እንዲያቀርብ ፣ ተከሳሾችን ማግኘት ካልቻለ ደግሞ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ትእዛዝ በመስጠት ለጥቅምት 9 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.