Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የመታወቂያ እድሳት በተያዘው ወር መጨረሻ ይጀመራል

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 4 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ታግዶ የቆየው የመታወቂያ እድሳት በተያዘው ጥቅምት ወር መጨረሻ እንደሚጀመር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ ዋና ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ ገለጹ።

በመዲናዋ በመታወቂያ አሰጣጥና እድሳት ዙሪያ ለተስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች ዘላቂ እልባት በመስጠት ችግሩን ለመፍታት አገልግሎቱ በጊዜያዊነት እንዲቆም መደረጉ ይታወሳል።

የከተማ አስተዳደሩ በብልሹ ተግባሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አመራሮችና ሰራተኞችን በመለየት ተጠያቂ የማድረግ ስራ ማከናወኑ ተገልጿል፡፡

ዋና ስራስኪያጁ በጉዳዩ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር በተገናኘ ህገ ወጥ ተግባር ሲፈፅሙ የነበሩ አመራርና ባለሙያዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተለይም ችግሩ ጎልቶ በታየባቸው 37 ወረዳዎች በተደረገ ክትትል 90 አመራሮችና ባለሙያዎችን ተጠያቂ የማድረግ ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።

ታግዶ የቆየው የመታወቂያ አድሳት ህጋዊ አሰራሩን ተከትሎ በተያዘው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ እንደሚጀመርም ነው የተገለጸው።

ከዚህ ጎን ለጎን የከተማዋ ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆንኑአሰራሩን የማዘመን ስራ ይቀጥላል ነው የተባለው፡፡

በአሁኑ ወቅት የራሳቸው መለያና ምሥጥራዊነት ያላቸው መታወቂያ ለመስጠት የሚያገለግሉ ወረቀቶች በመታተም ላይ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይ ለነዋሪው የመስጠት ተግባር ይከናወናል ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.