Fana: At a Speed of Life!

ለኢትዮጵያና የአፍሪካ ሀገራት ከሚሰራጩት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያዎች መካከል የመጀመሪዎቹ አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ)  የመጀመሪያው ዙር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ – ጃክ ማ ኢንሽዬቲቭ አማካኝነት ለኢትዮጵያ እና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከሚሰራጩት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያዎች መካከል የመጀመሪዎቹ ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።

የምርመራ ቁሶች እና የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎች የሚገኙባቸው እነዚህን ቁሳቁሶች በኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ነው እየተጓጓዙ ያሉት።

ድጋፉን በማስመልከት የድጋፉ ብሄራዊ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ ድጋፉ ኢትዮጵያ ዳግም በአህጉሪቱ መሪነቷን የተወጣችበት ነው ብለዋል፡፡

ድጋፉ ወደ ሀምሳ አራቱም የአፍሪካ ሀገራት ያለምንም ክፍያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያከፋፍል ይሆናልም ነው ያሉት፡፡

አያይዘውም የድጋፉ መሰረት ሰብዓዊነት ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያራምዱት የመደመር ፍልስፍና አህጉራዊ አቅምን በጋራ  ለመጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ትልቅ አየር መንገድ ያላት ኢትዮጵያ አፍሪካን ለመርዳት ከዚህ የተሻለ ጊዜም እንደሌላትም ዶ/ር ሹመቴ አስታውቀዋል፡፡

በድጋፉ ርክክብ ወቅት የተገኙት የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ አምባሳደር እና በኢትዮጵያ የጅቡቲ አምባሳደር ÷የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት ከጃክ-ማ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ይህንን ኢኒሼቲቭ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና የአሊ ባባ መስራች እና ባለቤት ጃክ ማ የአፍሪካ ሃገራት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለሚያደርጉት ጥረት የሚውል ድጋፍ ለማድረግና ለማሰራጨት  የዛሬ ሳምንት ማቋቋማቸው ይታወሳል፡፡

ድጋፉ ለ54 የአፍሪካ ሀገራት ቫይረሱን ለመከላከል ለሚያደርጉት ጥረት የሚውል የህክምና ቁሳቁስ መሆኑንም ጃክ ማ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

ድጋፉም በኢትዮጵያ አማካኝነት ለሁሉም የአፍሪካ ሃገራት ይዳረሳል ነው የተባለው።

በዚህ መሰረት ለእያንዳንዱ የአፍሪካ ሃገር ቫይረሱን ለመለየት የሚረዱ 20 ሺህ መመርመሪያዎች፣ 100 ሺህ የፊት ጭምብል፣ የህክምና ባለሙያዎች የሚለብሷቸው 1 ሺህ መከላከያ ልብሶች የሚከፋፈል ይሆናል።

ዛሬ የገቡት ቁሳቁሶችም በመላው ኢትዮጵያ እንዲሁም እንዲደርሳቸው ለታሰበላቸው የአፍሪካ ሀገራት እስከ ፊታችን ማክሰኞ ድረስ ተሰራጭተው ይጠናቀቃሉ ተብሏል።

ቀሪዎቹ ድጋፎችም በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የሚጠናቀቁ ይሆናል።

 

በአልአዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.