Fana: At a Speed of Life!

የነጭ ሽንኩርት የጤና በረከቶች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ነጭ ሽንኩርት በውስጡ በያዛቸው ንጥረ ነገሮች ለተለያዩ በሽታዎች ፍቱን እንዲሁም የጤና በረከት እንዳለው ይነገርለታል።

ነጭ ሽንኩርት ዝቅተኛ ካሎሪ ያለው የምግብ አይነት ሲሆን ፥ በቫይታሚን ሲ፣ ቫይታሚን ቢ6 እና ማንጋነዝ የበለፀገ ነው።

በከፍተኛ ደረጃ ባክቴሪያንና ቫይረስን የማጥፋት ብቃት ያለው የምግብ ዓይነት እንደመሆኑም የሰው ልጅ በእነዚህ በሽታ አምጪ ተህዋስያን እንዳይጠቃ ይከላከላል።

በነጭ ሽንኩርት ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገር በፈንገስ ምክንያት ለሚከሰቱ የቆዳ ሕመሞች መድኃኒትነት እንዳለው የሚነሳ ሲሆን የቆዳ ጤንነትን ለመጠበቅ ይረዳል፡፡

ነጭ ሽንኩርት በውስጡ ከያዛቸው ንጥረ ነገሮች መካከል የደም መርጋትን መከላከል የሚያስችል ንጥረ ነገር አንዱ ሲሆን ፥ የደም ግፊት መጨመርን ይከላከላል፡፡

ከዕድሜ መጨመር የተነሳ የሚከሰት የደም ቧንቧ ጥበትን የመከላከል ጥቅም ያለው ነጭ ሽንኩርት ፥ ይህንን በማድረግ በደም ቧንቧ ጥበት ምክንያት የሚከሰት የልብ ሕመም የመከላከል አቅምን ያሳድጋል፡፡

በተመሳሳይ በሰውነት ውስጥ ያለውን የኮሌስትሮል መጠን በመቀነስ በደም ቧንቧ ላይ የሚገኘውን የስብ ክምችት እንዲቀንስ በማድረግም ለጤና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

ሰውነት በአለርጂ እንዳይጠቃ የማድረግ አቅም ያለው ነጭ ሽንኩርት ፥ በሰውነት ላይ ለሚወጣና በአንዳንድ ነፍሳት ምክንያት የሚወጣን ሽፍታም ይከላከላል፡፡

ጉንፋን በተደጋጋሚ ለሚይዛቸው ሰዎችም ነጭ ሽንኩርትን መጠቀም መፍትሄ መሆኑን ኸልዝ ላይን ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ ባወጣው መረጃ አመላክቷል።

ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው በጉንፋን ከተያዘ በኋላም እንዳይበረታበትና ቶሎ እንዲያገግም እንደሚረዳም ነው የተገለጸው።

መረጃው አክሎም የነጭ ሽንኩርት በሰውነት ውስጥ የሚመነጨውን የኢንሱሊን መጠን በመጨመርና በደም ውስጥ የሚገኙትን የስኳር መጠን በመቆጣጠር የስኳር ሕመም ተጋላጭነትን ይቀንሳል ይላል፡፡

የጥርስ ህመምን ለማከም የሚረዳውን ነጭ ሽንኩርት በመፍጨት የጥርስ ህመም ባለበት ቦታ ላይ በማድረግ ባክቴሪያዎችን በማጥፋት የህመሙን ስሜት መቀነስ ይቻላል።

ነጭ ሽንኩርትን በዕለት ተዕለት አመጋገብ ውስጥ በማካተት የሰውነትን በሽታ መከላከል አቅምንና በበሽታ ሰውነት ከተጎዳ በኋላ በፍጥነት እንዲያገግም ለማድረግም ያግዛል።

ይሁን እንጂ ነጭ ሽንኩርትን በአመጋገብዎ ከማካተትዎ በፊት የነጭ ሽንኩርት አለርጂ እንደሌለብዎት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ነው የተነሳው፡፡

የደም መፍሰስ ችግር ካለብዎና መሰል የጤና ችግር አጋጥሞዎት መድሃኒቶችን እየወሰዱ ከሆነ ነጭ ሽንኩርት የተካተተበትን ምግብ ከመመገብዎ በፊት ሐኪም ማማከርወን አይዘንጉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.