Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ምዕራብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ከሱሪ እና ቤሮ ወረዳ ማህበረሰብ ጋር ተወየዩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ የተመራው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከሱሪ እና ቤሮ ወረዳ ማህበረሰብ ጋር ተወያየ።

ሱሪና የቤሮ ወረዳዎች ዋና አስተዳዳሪዎች አቶ ባርቱሬ ኦሌቻጊ እና አቶ ከበደ ቡርጂ ፥ የአርብቶ አደሩን ህብረተሰብ የኑሮ ሁኔታ ሊቀይሩ የሚችሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች እንዲዘረጉ ጠይቀዋል ።

በኪብሽና በጀባ ከተማ ከህዝቡ ጋር በነበረው ውይይት ፥ ነዋሪዎቹ የመንገድ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የድልድይና የጸጥታ ችግሮች እንዲቀረፉ አንስተዋል፡፡

አካባቢው ከፍተኛ የወርቅና ሌሎች ማዕድናት ያሉበት በመሆኑ ውጫዊና ውስጣዊ የጸጥታ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ የክልሉ መንግስት ትኩረት እንዲያደርግም ነው የጠየቁት።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምትኩ ታምሩ ፥ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራዎች መሠራታቸውን ተናግረው፥ ህዝቡ የሚያነሳቸው የመልማትና የጸጥታ ችግሮች እንዲፈቱ በየደረጃው ምላሽ ያገኛሉም ብለዋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው ፥ ወረዳው በእንስሳት ሀብት፣ ማርና ቡና እንዲሁም በወርቅ ማዕድን እንዲሁም ባልተበረዘ ቱባ ባህል በሚታወቁ ሱሪና ቤሮ ወረዳ ተገኝተው ውይይት በማድረጋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል ።

ህዝቡ አሁን ላይ ያነሳቸው የመልማት ጥያቄዎችና የጸጥታ ስራዎች በህዝቡ፣ በዞኑ መንግስትና በክልሉ መንግስት ደረጃ በደረጃ ይፈታሉ ብለዋል ።

ብሔራዊ የወርቅ ግብይት ስራና የወርቅ ማንጠሪያ ማሽን በወርቅ አምራቹ አቅራቢያ እንዲመቻች ጥረት ይደረጋል ማለታቸውን ከዲማ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከአጎራባች ክልሎችና ከደቡብ ሱዳን ጠረፍ አካባቢ ያሉ ችግሮች በሚፈቱበት ሁኔታ የተጀመሩ ስራዎች በክልሉና በፌዴራል መንግስት ትኩረት እንደሚሰጠውም አንስተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.