Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ላይ የተሞከሩ ከ1 ሺህ 600 በላይ የሳይበር ጥቃቶች ከሸፉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ በተለያዩ ተቋማት ላይ የተሞከሩ ከ1 ሺህ 600 በላይ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።

በመረጃና መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ጥቃት ትንተና ቡድን መሪ አቤል ተመስገን እንደተናገሩት ፥ ባለፉት ሦስት ወራት በኢትዮጵያ ላይ የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች አብዛኞቹ ዒላማቸው የፋይናንስና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ላይ ነው።

በኢትዮጵያ ሊደርስ የነበረውን አደጋ የማዳን አቅም እየጎለበተ መሆኑን የገለጹት ቡድን መሪው ፥ የሳይበር ወንጀል ኢ-ተገማች በመሆኑ ሁልጊዜም መጠንቀቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ተቋማት የራሳቸው የመቆጣጠሪያ ማዕከላት በማቋቋም የመከላከል ስራዎችን ሊሰሩ እንደሚገባም አስረድተዋል።

አስተዳደሩ የመንግስትና የግል ተቋማትን የማማከር አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።

ተቋማት የሳይበር ጥቃት በሚያጋጥማቸው ወቅት በአስተዳደሩ በኩል አስፈላጊውን ትንተና ሊያደርጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ተቋማት መሰል ጥቃቶች በሚያጋጥማቸው ወቅት በ933 ነጻ የስልክ መስመር ለአስተዳደሩ ሊያሳውቁ እንደሚገባም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተዳደሩ በተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት እንደደረሰ መረጃ ሲያገኝ ጥቃቱን ማን አደረሰው፣ ከየት ነው የደረሰው፣ ምን አይነት ክፍተቶች በተቋማቱ እንደነበሩ ትንተና ይሰራልም ነው ያሉት ቡድን መሪው።

በሰበሰበው መረጃ መሰረት የደረሱ የሳይበር ጥቃቶችን በመተንተን ችግሩንም መፍታት እንደሚቻል ተቋማት ሊረዱት እንደሚገባ ነው ያስረዱት፡፡

የሳይበር ምሕዳር በባህሪው ድንበር የለሽና ኢ-ተገማች በመሆኑ ዓለም በዚህ መጠነ-ሰፊና ተለዋዋጭ ወንጀል በየቀኑ በአማካይ 16 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ሀብት እንደምታጣ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.