Fana: At a Speed of Life!

ምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የጋራ ስምምነት ሠነድ ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መካከል የጋራ ስምምነት ሠነድ ተፈረመ፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት÷ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እና የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ሰብሳቢ መብራቱ አለሙ ናቸው፡፡

ስምምነቱ የተፈረመው ምክር ቤቱ መጋቢት 2011 ዓ.ም በፓርቲዎች መካከል የተፈረመውን የቃል ኪዳን ሠነድ ዓላማ ለማሳካት ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ቦርዱ ድጋፍ ለማድረግ እንዲችል ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የሚሰጠውን ድጋፍ በመግባቢያ ሠነዱ ውስጥ በተጣለበት ኃላፊነት መሠረት ለታለመለት ዓላማ ማዋሉን ለማረጋገጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚህ የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ቦርዱ ለምክር ቤቱ ድጋፍ ከሚያደርግባቸውና ከምክር ቤቱ ጋር የጋራ መግባባት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች ውስጥ÷ የምክር ቤቱ ገጽታ ግንባታ ሥራዎች (ለመጽሔት ዝግጅት፣ ለማስታወቂያና ተዛማጅ ሥራዎች )፣ ጋዜጣዊ መግለጫ ማዘጋጀት እና ለአስተዳደራዊ ወጪዎች ማለትም ለሥራ ፈጻሚዎች የሚውሉ የተለያዩ ወጪዎች ተግባራትን ለማከናወን የሚሆን ም/ቤቱ ወደ ክልል የጋራ ም/ቤቶች ለድጋፍና ክትትል ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የሚደረግ ወጪን መሸፈን የሚሉት ይጠቀሳሉ።

ቦርዱ ቀደም ሲል በሕግ በተሰጠው ሥልጣንና ኃለፊነት የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመከታተል እና የመደገፍ ኃላፊነት ያለበት እንደመሆኑ÷ ለእያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ የሆነውን ምክር ቤት በመደገፍ የበለጠ ተደራሽ እና ፓርቲዎች በዴሞክራሲ ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት መስፈን እና በሰላም መረጋገጥ ላይ ያላቸውን ሚና የበለጠ ለማጎልበት በማሰብ ለጋራ ምክር ቤቱ ቢሮና አስፈላጊ የቢሮ ቁሳቁሶችን እንዲሁም ለሥራ እንቅስቃሴ የሚረዳ የመኪና ድጋፍ ማድረጉ ይታወቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.