Fana: At a Speed of Life!

ለመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሃይጅን ፕሮግራም ውጤታማነት የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተቋማት መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሠራር የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሃይጅን ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን ማስቻሉ ተገለጸ፡፡

በጋና አክራ እየተካሄደ በሚገኘው “All System Go Africa” ሲምፖዚየም ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ በፓናል ውይይት ወቅት እንደገለጹት÷ በኢትዮጵያ ለመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን ፕሮግራም ውጤታማነት የመንግሥት ቁርጠኝነትና በተቋማት መካከል የተፈጠረው ቅንጅታዊ አሠራር ተጠቃሽ ነው፡፡

በዚህም በውሃ፣ በትምህርት፣ በጤና እና በፋይናንስ ዘርፍ መካከል ያለው ቅንጅት የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን ፕሮግራም አተገባበር ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በክልል ደረጃ የሚተገበሩ ለመጠጥ ውሃ ግንባታ የሚውል የተዘዋዋሪ ብድር አገልግሎት መጀመር በዘርፉ ሌላው በጥሩ ተሞክሮነት የሚጠቀስ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

የዘርፉን የልማት ግቦች በ2030 ለማሳካት በሃብት ማሰባሰብ፣ የዘርፉን ፖሊሲዎች በመከለስ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር፣ ሀገር በቀል የውሃ መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እንዲሁም ከልማት ድርጅቶችና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ትብብርና ድጋፍን በማጠናከር ላይ ትኩረት በማድረግ ግቡን ለማሳካት እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡

ሲምፖዚየሙ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት በመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሃይጅን አገልግሎት አቅርቦትና ስርዓት ላይ የሚመክር ሲሆን÷ የየሀገራቱ የውሃና ሳኒቴሽን ሚኒስትሮች፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የለጋሽ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ተመራማሪዎች፣ በዘርፉ ያሉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ይሳተፉበታል፡፡

ሲምፖዚየሙ የጋና መንግሥት፣ ዩኒሴፍ እና አይ.አር.ሲ ዋሽ በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን÷ እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2022 የሚቆይ መድረክ ነው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.