Fana: At a Speed of Life!

ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ሥርዓት በመገንባት የተጋላጭነትን ምንጭ ማድረቅ የዛሬው ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው – ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ሥርዓት በመገንባት የተጋላጭነትን ምንጭ ማድረቅ የዛሬው ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
 
ርዕሰ መስተዳድሩ ጉዳዩን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ÷ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን በውድ መስዋዕትነት በማስከበር የግዛት አንድነቷን ጠብቃ የኖረች የአፍሪካ የነፃነት ዓርማ ናት ብለዋል።
 
ይሁን እንጂ ሀገራችን በጦር ሜዳ ስታስመዘግብ የኖረችውን አንፀባራቂ ድል በሌሎች ዘርፎች ባለመቀዳጀቷ ተጋላጭነቷ አይሎ ታሪካዊ ጠላቶቿ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የቤት ስራዋን በማብዛት በግጭት አዙሪት እንድትዳክር፣ በስንዴ ልመና ድሏ እንዲደበዝዝ፣ እጇንም ለመጠምዘዝ ሲታትሩ ይታያል ነው ያሉት።
 
የኦሮሚያ የክልል ህዝብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በክልሉ ያሉትን መልካም እድሎች በመለየትና የምርት ሀይሎችን በማቀናጀት በተለይም በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በመቅረፅ ሰፋፊና ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛልም ብለዋል።
 
በመከናወን ላይ በሚገኙ የልማት ስራዎችም የህዝቡን ኑሮ የሚቀይሩ እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ሲሉም ገልጸዋል።
 
በክልሉ እየተተገበሩ ካሉት ኢኒሼቲቮች መካከል አንዱና ዋነኛው የበጋ የመስኖ የስንዴ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ ባለፈው ዓመት የተገኘው ውጤት ከራሳችን አልፈን ሌሎችን መመገብ እንደምንችል ያረጋገጠልን አጋጣሚ ነው ብለዋል።
 
የርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል ፡-
 
ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ሥርዓት በመገንባት የተጋላጭነታችንን ምንጭ ማድረቅ የዛሬው ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው!
 
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን በውድ መስዋዕትነት በማስከበር የግዛት አንድነቷን ጠብቃ የኖረች የአፍሪካ የነፃነት ዓርማ ነች። ነገር ግን አገራችን በጦር ሜዳ ስታስመዘግብ የኖረችውን አንፀባራቂ ድሎች በሌሎች ዘርፎች ባለመቀዳጀቷ ተጋላጭነቷ አይሎ ታሪካዊ ጠላቶቿ ይሄን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የቤት ስራዋን በማብዛት በግጭት አዙሪት እንድትዳክር፣ በስንዴ ልመና ድሏ እንዲደበዝዝ፣ እጇንም ለመጠምዘዝ ሲታትሩ ይታያል።
 
የሆነው ሆኖ ግን ሉዓላዊነቱንና ነፃነቱን በደሙ አስከብሮ የኖረ ህዝብ ስለምን ምጽዋት ከባዕዳን ይጠብቃል? በክብር ካባ ላይ እንደምን ውርደትን ተሸክመን ዘለቅን? ይሄ የውርደት ምዕራፍ በዚህ ትውልድ ሊዘጋ ይገባል።
 
ባለፉት አራት የለውጥ ዓመታት ይህንን የተቃርኖ ምዕራፍ ለመዝጋትና ነፃነታችን የተሟላ እንዲሆን የተጋላጭነታችን ምንጭ የሚቀርፍ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
 
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም የክልሉን ህዝብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በክልሉ ያሉትን መልካም እድሎችን በመለየትና የምርት ሀይሎችን በማቀናጀት በተለይም በግብርናዉ ዘርፍ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በመቅረፅ ሰፋፊና ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
 
በመሆኑም በመከናወን ላይ የሚገኙ የልማት ስራዎችም የህዝባችን ኑሮ የሚቀይሩ እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።በክልላችን እየተተገበሩ ካሉት ኢኒሼቲቮች መካከል አንዱና ዋነኛው የበጋ የመስኖ የስንዴ ሲሆን ባለፈው ዓመት የተገኘው ውጤት ከራሳችን አልፈን ሌሎችን መመገብ እንደምንችል ያረጋገጠልን አጋጣሚ ነው።
 
የዝናብ ጥገኛ ሆኖ የቆየውን የግብርና ስራችንን በመቀየር ክረምት በዝናብ፤ በጋ በመስኖ በዓመት ሁለት ሶስቴ በማምረት አንደኛ የስራ ባህላችንን ማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የቻልን ሲሆን÷ በሌላ በኩል ደግሞ በደም ጠብቀን ያቆየነውን ሉዓላዊነታችንን በላባችን ማጽናት እንደምንችል ያሳየንበት ነው። ይሄ ትልቅ የታሪክ እጥፋት እንደመሆኑ መጠን የዚህ ትውልድ አሻራ ነው።
 
ባሳለፍነው ዓመት ህዝባችንን ከጫፍ ጫፍ በማንቀሳቀስ በበጋ ስንዴ እንዲያመርት በማድረግ ከውጭ ሲገባ የነበረውን ሀገር ውስጥ በማምረት መተካት ችለናል። በያዝነው የበጀት ዓመትም በመኸር በመስኖ ስንዴን በማምረት የሀገር ውስጥ ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል። በዘንድሮ የመኽር እርሻ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በስንዴ የተሸፈነ ሲሆን ÷ በበጋዉ ደግሞ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት በስንዴ ለመሸፈን በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
 
የክልላችን ህዝብ ትላንት የሀገራችን ሉዓላዊነት በማስከበር በግንባር ቀደምትነት ሲሳተፍና መስዋዕትነት ሲከፍል እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረገው ዘርፈ ብዙ ርብርብ ውስጥ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እያደረገ ያለው አበርክቶ የሚያኮራ ነው። ለዚህም የክልሉ መንግስት ታላቅ አክብሮት ያለው ሲሆን በዚህ ዓመት የተያዘውን እቅድ ለማሳካትም ተሳትፏችንን ይበልጥ ማጎልበት እንደሚገባን በክልሉ መንግስት ስም ጥሪዬን ማቅረብ እወዳለሁ።
 
የዛሬው ትውልድ ስለ ኦሮሚያ ለምነትና ለምለምነት ማውሳትና ማወደስ ብቻ ሳይሆን የተራቆቱ ተራራዎቿን በማልበስ አሻራውን ማኖር፣ ቆላና ደጋዋን በማልማት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ መሆን አለበት። ስለሆነም ትግላችን ዘርፈ ብዙ እንደመሆኑ መጠን፣ ድላችንን ሁለንተናዊ ለማድረግ ትላንት በውድ መስዋዕትነት ያስከበርነውን ነፃነታችንን በላባችን ለማጽናት መትጋት ይኖርብናል።
 
ሽመልስ አብዲሳ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር
 
ጥቅምት፣ 2015 ዓ.ም
 
ፊንፊኔ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.