Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ የበካይ ጋዝን በሚያስቀር የዘመናዊ ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ዓለም አቀፍ ውድድር አሸነፈች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ከተማ የበካይ ጋዝን በሚያስቀር የዘመናዊ ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት በመዘርጋት ባከናወነችው መልካም ስራ በሲ40 የከንቲባዎች ፎረም አሸናፊ ሆነች፡፡

ሽልማቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ በአካል ተገኝተው ተቀብለዋል፡፡

የሲ40 የዓለም ከንቲባዎች ፎረም በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ ከተማ እየተካሄደ ነው።

አዲስ አበባ ከተማም የአየር ንብረትን የሚከላከል ተስማሚና መልሶ የመጠቀም አሰራርን የተገበረና የያዘ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት በመዘርጋት ለአረንጓዴና ጤናማ የከተማ ግንባታ ሂደትና ቆሻሻን ወደ ኮምፖስት በመቀየር ለገቢ ማስገኛ ስራ በማዋል ጉልህ ድርሻ በማበርከት በመልካም ተሞክሮ ነው የተሸለመችው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም የነበረውን ለበካይነት የተጋለጠ አሰራር በማስቀረት በቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት የብዙዎችን ህይወት ሊታደግ የሚችልና በካይ ፎሲል ጋዝ ልቀትን ያስቀረ፣ ተመልሶ በከተማ እየተከናወነ ላለው የጓሮ አትክልት ልማት ስራ ማዳበሪያ ማቅረብ ያስቻለ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት መዘርጋቱ ለእውቅና እንዳበቃው ተጠቅሷል፡፡

በዚህ ስራ የበርካታ ወጣቶችን ገቢ ከማሳደጉም በላይ ተፈጥሮን የሚያክምና ቆሻሻን ወደ ሃብትነት የቀየረ በመሆኑ ከብዙ ትላልቅ የዓለም ከተሞች ከቀረቡ ተሞክሮዎች ጋር በመወዳደር አሸናፊ በመሆን ሽልማቱን ማግኘት ተችሏል።

የሲ40 የዓለም ከንቲባዎች ፎረም ከተሞች የአየር ንብረት ከካርበን ዳይኦክሳይድ ልቀትና ለዓለም ከተሞች የሙቀት መጨመር ምክንያት የሆነው ግሪንሃውስ ጋዝ ተፅእኖ በጋራ ለመከላከል የተመሰረተ የ100 ከተሞች ጥምረት መሆኑን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

አዲስ አበባ ከቀናት በፊት በተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሪዮ የእውቅና ሽልማት ማግኘቷ ይታወሳል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.