Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ዲፕሎማሲ የወጣቶች ልዑክ በሞቃዲሾ  የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አከናወነ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ዲፕሎማሲ የወጣቶች ልዑክ በሶማሊያ፣ ሞቃዲሾ  የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አከናወነ።

በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር  አምባሳደር ጀማሉዲን ሙስጠፋ   የተመራው ልዑክ ትናንት ሞቃዲሾ መግባቱን ተከትሎ፥ የልዑካን ቡድኑ አባላት ዛሬ  ከኢትዮጵያ የወሰዷቸውን ችግኞች በሶማሊያ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተክለዋል።

የልዑካን ቡድኑ መሪና በሶማሊያ የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር ጀማሉዲን፥ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ቀደም ሲል ያበረከተችውን አበርክቶ አንስተዋል።

አሁን ደግሞ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባትና በሀገር ውስጥ የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ የማስፋቱ አካል የሆነውን ችግኝን የመትከልና ወንድማማችነትን የመፍጠሩ ስራ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በሶማሊያ  የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር  አብዱልፈታህ አብዱላሂ በበኩላቸው፥ ከኢትዮጵያ የመጡት 500 ችግኞች የሁለቱን ሀገራት በፀጥታና በደህንነት ላይ የነበረ ግንኙነት በልማትና በኢኮኖሚ የመተሳሰር ምልክት ሆነው በኢትዮጵያዊያን እና በሶማሊያ ወጣቶች ተተክለዋል ብለዋል ።

“ለወጣቶች ከአባቶቻችን የተረከብናትን አለም ማስረከብ አለብን” ያሉት የሶማሊያ የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ድኤታ አደም ኢብራሂም ሂርሴ፥ ሀገራቸው በየዓመቱ የድርቅ አደጋ ተጠቂ መሆኗን ተናግረዋል ።

ከትናንት በስቲያ በሶማሊያ ፕሬዚዳንት ለተጀመረው የአረንጓዴ ሶማሊያ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር እና የአየር ንብረት ለውጥን የመመከት ጅምር ስራ የልዑካን ቡድኑ  አበርክቶ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ወጣቶች በጋራ የተሳተፉበት የፓናል ውይይትም ተካሂዷል ።

ወጣቶቹ ግንኙነታቸውን ቀጣይ የሚያደርጉበት የማህበራዊ ትስስር ገፅ ቡድንም ፈጥረዉ  እንቅስቃሴዎችን ማስቀጠል ጀምረዋል ።

በፀጋዬ ወንድወሰን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.