Fana: At a Speed of Life!

የዕድገታችን ቁልፍ በእጃችን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዕድገታችን ቁልፍ በእጃችን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፥ ወደ ብልጽግና የምናደርገው ጉዞ የተሣለጠ የሚሆነው በዋናነት በውስጣዊ ዐቅማችን ላይ ከተመሠረተ ነው ብለዋል፡፡

ውስጣዊ ዐቅማችን ማለት፥ የሕዝባችን ዐቅም፣ የሀገራችን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሀብት እንዲሁም የአዲሱ ትውልድ የፈጠራ ክህሎት ናቸው ብለዋል።

በአስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ እያለፍን እንኳን ችግር ተቋቋሚ ኢኮኖሚ ሊኖረን ችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ በመጠኑም ቢሆን ያሉንን ውስጣዊ ዐቅሞች አሟጠን ለመጠቀም መነሣታችን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከየትኛውም ወገን የሚሰጠን ድጋፍ በውስጣዊ ዐቅማችን ላይ ተጨማሪ እንጂ ዋና የዕድገት ምንጭ ሊሆን አይችልም ብለዋል።

ውስጣዊ ዐቅማችንን ተጠቅመን ወደ ብልጽግና የምናደርገው ጉዞ ከዕንቅፋቶች የጸዳ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ ሌብነትና ምርት ሥወራ ዋነኞቹ ፈተናዎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በዚህም ወደ ውጭ መላክ የሚገባውን ምርት መደበቅ፣ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሬ ዝውውርና መሬትን በአሻጥር መውረር በቆራጥነት ፈጣን እርምጃ ልንወስድባቸው የሚገቡ የብልጽግና ዕንቅፋቶች ናቸው ብለዋል።

በቀጣይ ፈተናዎችን የሚሻገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እንድንችል ሁለት መልክ ያሉት ትግል ያስፈልገናል። ማጥፋት እና ማልማት ነው ያሉት።

የኢኮኖሚ አሻጥሮችን፣ ሌብነትንና ምርት ሥወራን ለማጥፋት የሁሉንም ወሳኝ ትግል እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ገቢን የመጨመርና ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነስ የልማት ትግል ይጠበቅብናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፥ እነዚህ ሁለቱ የትግል መስኮች በራሳችን ፖሊሲና በራሳችን ዐቅም ማደግ እንድንችል ያስችሉናል፤ የዕድገታችን ቁልፍ በእጃችን ነውና ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.