Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በቴክኖሎጂ የታገዘ መረጃን ተደራሽ የሚያደርግ ግብረ ኃይል ተቋቋመ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ አሰጣጥ እና ስርጭት እንዲኖር ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ግብረ ኃይል በማቋቋም ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ የግብረ ሀይሉ ሰብሳቢ እና የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።

በወረርሽኙ ዙርያ መረጃ ሲሰጥ የነበረውን 8335ን በማጠናከር ከ36 በላይ የጥሪ መልስ የሚሰጡ የጥሪ ማዕከላትን በማሳደግ እና ከዚህ በፊት ለኤች አይ ቪ ኤድስ ትምህርት መስጫ የጥሪ ማዕከልነት ሲያገለግል የነበረውን 952ን ለኮሮና ቫይረስ መረጃና ትምህርት ሰጭ ማዕከልነት ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ማንኛውንም አይነት ወረርሽኙን የሚመለከት መረጃን ህብረተሰቡ 444 ላይ በመደወል በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲያገኝ በመደረግ ላይም መሆኑም ተገልጿል።

በተጨማሪም በተለያዩ ቋንቋዎች በክልሎች መረጃ የሚሰጡ የጥሪ ማዕከላት 6599 ለደቡብ ክልል፣ 6244 ለትግራይ ክልል፣ 6955 ለኦሮሚያ ክልል፣ 6407 ለድሬደዋ፣ 6982 ለአማራ ክልል ተዘጋጅተዋልም ነው የተባለው።

ዶክተር አብርሃም የትምህርት እንቅስቃሴውን ከመደገፍ አንጻር ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸው በየክፍሎቻቸው ሆነው የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ተጠቅመው ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት አሰራር መፍጠር የሚያስችል ስራ መሰራት አለበት ብለዋል።

የክፍያ ስርዓትን በተመለከተ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ከሚሰጡ ትምህርቶች በተጨማሪ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ክፍያ መፈጸም በሚቻልባቸው አሰራሮች ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ለመተግበር አማራጮች እንዲቀርቡ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ግብረ ኃይሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የቴክኖሎጂ ቡድን፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተውጣጣ ነው።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.