Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ ወታደሮቿን በዩክሬን ድንበር ማስፈሯን ተከትሎ ሩሲያ አጸፋዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል አስጠነቀቀች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ወታደሮቿን በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ማሰማራቷን ተከትሎ ሩሲያ አጸፋዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል አስጠነቀቀች፡፡

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ÷ በአሜሪካ ጦር 101ኛ የአየር ወለድ ብርጌድ የሚገኙ ወታደሮች በሮማኒያ (በዩክሬን ድንበር) መሰማራታቸውን ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ ወታደሮች በስፋራው መሰማራታቸውም ለሩሲያ ሰላም እና ደህንነት ከፍተኛ ስጋት መሆናቸውን ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡

የአሜሪካ ወታደሮች በዩክሬን ድንበር መሰማራት ለሩሲያ ከፍተኛ አደጋ አለው ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ሞስኮ ድርጊቱን በቀላሉ እንደማታየው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ስለሆነም ሩሲያ የተደቀነባትን ስጋት ለማስወገድ አስፈላጊውን አጸፋዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ነው ያስጠነቀቁት፡፡

አሜሪካ በአካባቢው የምታከናውነው መሰል አላስፈላጊ ትንኮሳም ለቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንቅፋት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በአሜሪካ ጦር የ101ኛ አየር ወለድ ብርጌድ አዛዥ በበኩላቸው፥ 4 ሺህ 700 የሚደርሱ ወታደሮች በዩክሬን ድንበር (በሮማኒያ) መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡

ወታደሮቹ በአካባቢው ከሚገኙ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባላት ጋር የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸውንም አንስተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ወታደሮቹ የሩሲያጦር በአካባቢው የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በትኩረት እንደሚከታተሉ መጠቆማቸውን አርቲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.